ሳምሰንግ በ3 ወራት፣ 8.8 ቢ. ዶላር አትርፏል

0
217

ካለፉት 3 አመታት ትርፉ ከፍተኛው ነው ተብሏል

ያለፉትን ወራት በእሳት ፈጣሪው ምርቱ በጋላክሲ ኖት 7 ሳቢያ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቆ የገፋው ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ፤ ባለፉት ሶስት አመታት ታሪኩ ከፍተኛው የተባለውን የ8.8 ቢሊዮን ዶላር የሩብ አመት ትርፍ ማስመዝገቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ እስካለፈው መጋቢት ወር ባለው ያለፈው ሩብ አመት ከፍተኛ የተባለውን ትርፍ ሊያስመዘግብ የቻለው፣ የሚሞሪ ቺፕስ፣ የቴሌቪዥን ፍላት ስክሪን እና የሞባይል ስልክ ምርቶቹ በተጠቃሚዎች ዘንድ ያላቸው ተፈላጊነት በመጨመሩ ነው ተብሏል፡፡
ኩባንያው በቀጣይም ትርፋማነቱን ከፍ አድርጎ እንደሚዘልቅ ይጠበቃል ያለው ዘገባው፣ ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው ከሰሞኑ ለገበያ ያቀረባቸው የጋላክሲ ኤስ 8 እና ኤስ 8 ፕላስ የሞባይል ምርቶቹ በገበያው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸው ነው መባሉን ገልጧል፡፡
ሳምሰንግ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ለገበያ ያቀረበው የጋላክሲ ኖት 7 ምርቱ፣ ባትሪው ከፍተኛ ሙቀትና እሳት እየፈጠረ አደጋ ማስከተሉን ተከትሎ ህልውናውን ስጋት ላይ የሚጥል ፈተና ውስጥ ገብቶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ለደምበኞቹ ሽጧቸው የነበሩ 2.5 ሚሊዮን ያህል ምርቶቹን መልሶ መረከቡ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳስከተለበትም አስታውሷል፡፡

ምንጭ =አዲስ አድማስ