ሸዕባን ሆይ እንኳን ደህና መጣህልን!

ሸዕባን ሆይ እንኳን ደህና መጣህልን!

0 6237

ሸዕባን ሆይ እንኳን ደህና መጣህልን!

ጊዜው ይሮጣል… ዕድሜያችንም እንደዚያው ይሮጣል፡፡ ዐጃኢብ በሚያሠኝ መልኩ በርካታ ቀናት አለፉ፣ ወራትም በተከታታይ ነጎዱ፡፡ እነሆ የተባረከው  የረመዳን ወር ቀናት ፊትለፊታችን ተደቅነዋል፣ ምርጡ ወርም ሽታው አዉዶናል፡፡

ሸዕባን የታላቁ ረመዳን ወር መግቢያ ላይ ያለ ወር ነው፡፡ የሰው ልጅ የዓመት ሥራዎች የሚገመገሙበት እና ለአላህ (ሱ.ወ.) የሚቀርቡበት ወርም ነው፡፡ ታላቁ ዓሊም ኢብኑ አልቀይም አልጀዉዚ (አላህ ይዘንላቸው) እንዲህ ብለዋል – ‹የአላህ ባሮች ሥራዎች አላህ ዘንድ የሚቀርቡት በሸዕባን ወር ዉስጥ ነው፡፡ ሰኞ እና ሀሙስ የሳምንት ሥራዎች አላህ ዘንድ የሚቀርቡት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የየዕለት ሥራዎች ደግሞ በቀናት መጨረሻዎች ላይ አላህ ዘንድ ይቀርባሉ፡፡ የየለሌሊት ሥራዎች ደግሞ ከንጋት በፊት ይቀርባሉ፡፡ የሰው ልጅ የምድር ላይ ዕድሜ ያበቃ እንደሆነ የህይወት ዘመን ሥራ በሙሉ ወደ ላይ ይወጣል፤ በመጨረሻም የአንድ ሰው የሥራ ፋይልም ይዘጋል፡፡›

ስለሆነም ሸዕባን የሰው ልጅ የዓመት ሥራ በጀት የሚጠናቀቅበት ወር ይመስላል፡፡ ዓመቱን በመልካም ሁኔታ ያሳለፈ ደስ ይበለው፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከወራት ሁሉ በተለየ መልኩ የሸዕባንን ወር በብዛት ይፆሙ ነበር፡፡ ከእናታችን ዓኢሻ (ረ.ዐ.) እንደተወራው ‹የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) የሸዕባንን ወር አብዛኛውን ይፆሙ ነበር፡፡› ብለዋል፡፡

በሌላም ሐዲሥ ‹ሙሉውን አሊያም ጥቂቱ ብቻ ሲቀር ይፆሙ ነበር፡፡› ብለዋል፡፡

ስለሆነም የሸዕባንን ወር መፆም የሚወደድ ነው፡፡ ምክንያቱም የነብያችን ፈለግ ነውና፡፡ ሆኖምግን ከረመዳን አጋማሽ በኋላ እና ሸዕባን ሊያልቅ አካባቢ ለረመዳን አንድ እና ሁለት ቀን ሲቀረው እንዳንፆም ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ከልክለዋል፡፡ በፊት የሱና ፆሞችን ማለትም ሰኞ እና ሐሙስን ይፆም የነበረ ሰው ሲቀር፡፡ ለምሳሌ የመጨረሻው የሸዕባን ቀን ሰኞ አሊያም ሐሙስ ላይ ቢዉል አንድ ሰው ቢፆም ችግር የለውም፡፡ የፆመው በምክንያት ነውና፡፡

ዑለማኦች እንደሚሉት ከረመዳን አንድ እና ሁለት ቀን አስቀድሞ መፆም የተከለከለበት ምክንያት ረመዳንን እና ሸዕባንን ግልጽ ባለ መልኩ ለመለየት እንዲቻል ነው፡፡

የሸዕባን ወር አጋማሽ ፆም

የሸዕባንን ወር አጋማሽ ስለመፆም የተነገሩ ዘገባዎች አሉ፡፡  እነኚህ ሐዲሦች ደካማ መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ በዚህ ዙሪያ የተነገረ አንድም ጠንካራ ሐዲሥ የለም፡፡ እንደማንኛውም ወር ሁሉ ከየወሩ ሦስት አጋማሽ ቀናትን ማለትም 13ኛ፣ 14ኛ እና 15ኛውን ቀን መፆም ይቻላል፡፡ እነኚህ ቀናት አያም አልቢድ ይባላሉ፡፡ እነርሱም ጨረቃ ደምቃ የምትታይባቸው ቀናት ናቸው፡፡ ስለሆነም ከደካማ  ሐዲሥ መረጃነት በሸዕባን ወር አጋማሽ ላይ የሚደረጉ ልዩ የአምልኮ ተግባራት ዉድቅ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

የሸዕባን ወር ፆም ትሩፋቶች

ከአቢ ሁረይራ (ረ.ዐ.) እንደተወራው ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በሆነ ወር ዉስጥ እንደሚፆሙት ሌላውን ወር ሲፆሙ አይቼ አላውቅም› አልኳቸው አለ፡፡ እርሣቸውም ‹የትኛው ወር ነው?› አሉት፡፡ ‹ሸዕባን› አልኳቸው አለ፡፡ እርሣቸውም (ሰ.ዐ.ወ.) ‹ሸዕባን በረጀብ እና በረመዳን መካከል ያለ ወር ነው፡፡ ሰዎች ከርሱ ይዘናጋሉ፡፡ የባሮች ሥራዎች ለአላህ የሚቀርቡበት ነው፡፡ ፆመኛ ሆኜ ሥራዬ አላህ ዘንድ እንዲቀርብ ስለምሻ ነው፡፡› አሉ፡፡

የሸዕባን ወር ፆም ከፊት ለፊቱ ለሚመጣው የረመዳን ወር ፆም ማለማመጃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ወደ አንድ ሥራ መግባት ሲፈልግ ደርቆ የከረመ ሰውነቱን እንደሚያሟሙቀው ሁሉ ወደ ረመዳን ከመግባቱ በፊት ሸዕባንን መፆሙ የረመዳን ወር ፆም እንዳይከብደው ያግዘዋል፣ አስቀድሞ ስለተለማመደ ድካም አያገኘውም ብርታት ይኖረዋል፣ በተነቃቃ መንፈስም ወሩን ይጾማል፡፡ ስለሆነም ለሚመጣው ረመዳን ካሁኑ ነፍስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፣ ከፆም በተጨማሪ በመልካም ሥራ ላይ ራስን ማለማመድ በጎ ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን  ነፍስ ማንኛውም ሥራ ይገራላት ዘንድ ከወዲሁ ማለማመድ ተገቢ ነው፡፡

ቀደምት ደጋግ ሰዎች ስለ ሸዕባን ወር ምን አሉ?

ኢብኑ ረጀብ እንዲህ ይላሉ – ‹ሸዕባን ወር የረመዳን ወር መግቢያ እንደመሆኑ መጠን በረመዳን ዉስጥ የተደነገገው ፆም ለሸዕባን  ተደነገገ፡፡ ቁርኣንን ማንበብም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ለረመዳን ዝግጅት ይረዳል፣ ነፍስ ሥልጠና ታገኛለች፡፡ የአላህ ትዕዛዛቶችም ይገሩላታል፡፡›

ሰለመህ ኢብኑ ኩሀይል ‹ሸዕባን ወር የቁርኣን ቃሪኦች ወር ነው› ይባል ነበር ብለዋል፡፡

ዐምር ኢብኑ ቀይስ ሸዕባን ወር የገባ እንደሆነ ሱቁን ይዘጋና ወደ ቁርኣን ፊቱን ያዞራል፡፡

አቡበክር አልበልኺ ደግሞ አንዲህ ይላል- የረጀብ ወር እንደ ዳመና አምጭ ነፋስ ነው፣ የሸዕባን ወር ደግሞ እንደ ዳመና ሲሆን ረመዳን ደግሞ አንደ ዝናብ ነው፡፡ በረጀብ ወር ዉስጥ ያልዘራ እና ያልተከለ በሸዕባን ዉስጥ ደግሞ የዘራዉን ያልተንከባከበ፣ በረመዳን ዉስጥ ምርቱን ማጨድ አያስብ፡፡›

አዎን ቀደምቶች በዚህ መልኩ ነቅተው ለረመዳን ይዘጋጁ ነበር፡፡ እኛስ እንዴት ተዘጋጅተን ይሆን?  ሰዎች በሚዘናጉበት ወቅት መንቃት ብልህነት ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ሸዕባን ላይ የመፆማቸው ሚስጢር ሰዎች ስለሚዘናጉ መሆኑን ተናግረዋል፣ ፆም ደግሞ ምርጥ የአምልኮ ተግባር ነው፡፡ እርሣቸው ወንጀል የሌለባቸው ከመሆናቸው ጋር እንዲህ ይላሉ፡፡

እነሆ በአላህ ችሮታና ፈቃድ ረመዳን በር ላይ ደርሰናል፡፡ ቀደምቶቹ ደጋጎች አላህ (ሱ.ወ.) ለረመዳን ያደርሣቸው ዘንድ ከብዙ ወራት በፊት አብዝተው ይማፀኑ ነበር፡፡ ረመዳን ታላቅ ወር ነውና፡፡ ወሩ ደርሰው ለመፆም ያልታደሉም ብዙ ናቸው፡፡ ለሸዕባን ወር ስላደረሰን አላህን (ሱ.ወ.) አብዝተን እናመስግን፡፡ ለረመዳን ያደርሰን ዘንድም አምላካችንን እንማፀን፡፡

እንዲሁ እንደዋዛ ረጀብ አለፈ፣ ሸዕባን መጣ፣ ረመዳንም ሽታው አወደን፡፡ ስለሆነም ከወዲሁ ዝግጅት ያስፈልገናል፡፡ ሥራችን አላህ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ በንፁህ ልብ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) መመለስ ይኖርብናል፡፡

www.alifradio.com

 

 

 

SIMILAR ARTICLES

0 4485