በረመዳን ተውባ ለምን?

በረመዳን ተውባ ለምን?

0 4590

በረመዳን ተውባ ለምን?

ሙስሊም በመሰረቱ ሁሌም ተውባ ማድረግ አለበት፡፡ በየቀኑ፣ በየደቂቃና ሰከንዱ ወደ ጌታው መመለስ አለበት፡፡ ተውባ ማለት  አጥፍቻለሁ ዳግመኛ አይለምደኝም በማለት ወደ አላህ መመለስ ነው፡፡ ተውባ ጥፋትን ማመን፣ በሳለፉት ጥፋት መፀፀትና ዳግም ላለማጥፋት ቁርጠኛ ሀሳብ ማኖር ነው፡፡ የተውባ ዓላማው ለመሻሻል ነው፡፡ ከወንጀል ወደ ፅድቅ፣ ከጥፋት ወደ ልማት መምጣት ነው፡፡

ተውባ በእስልምናችን ግዴታ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሆኖ የማያጠፋ ማንም የለምና ሁሉ ተውባ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ተውባ የአላህ ነቢያትና የደጋግ ሰዎች መንገድ ጭምር ነው፡፡ ብዙዎች ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ስህተታቸው ወደ አላህ ተመልሰዋል፣ አላህም ተውባቸውን ተቀብሏቸዋል፡፡ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) በመመለስ ረገድ አባታችን አደም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ የተከለከሉትን ዛፍ በበሉ ‹ጌታችን ሆይ ነፍሳችንን በድለናልና አንተ ባትምረንና ባታዝንልን ከከሳሪዎች እንሆናለን› በመላት ነበር ወደ አላህ (ሱ.ወ.) የተመለሱት፡፡  የኛው አርዓያና ሞዴል የሆኑት ታላቁ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) ‹እኔ በቀን ዉስጥ ከሰባ ጊዜ በላይ ከአላህ ምህረትን እለምናለሁ፣ ወደርሱም እመለሳለሁ፡፡› ይሉ ነበር፡፡

በየቀኑ፣ በየደቂቃና ሰከንዱ ወደ አላህ መመለስ የቻለ ሰው መልካም፡፡ አላህ ይጨምርለት፡፡ ተዘናግቶ የከረመውን ደግሞ አላህ መዘናጋቱን ያንሳለት፡፡ አላህ ሁላችንንም ይመልሰን፡፡ ለእውነተኛ ተውበትም ይወፍቀን፡፡

ረመዳን ሲደርስ ብዙ ሰዎች ወደ አላህ መንገድ ይመለሳሉ፣  ወደ መስጊድ ፊታቸውን ይመልሳሉ፣ ወደፈጠራቸው አምላክ  ልቦናቸውን ያዞራሉ፡፡ ረሐረመቱን ከጅለው ነው የሚመጡት፣ እሱ ያከበረውን ወር አክብረው ነው የሚመለሱት፡፡ ስለሆነም ለምን መጣችሁ ተብለው መወቀስ የለባቸውም፣ መስጊድ ቢመጡም ሆነ መልካም ነገር ላይ ቢሳተፉ የጎሪጥ መታየት የለባቸውም፡፡

ረመዳን የተውባ ወር ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ወር ዉስጥ ተውባችንን ይበልጥ ማደስ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ወሩ የአላህ (ሱ.ወ.) እዝነት በስፋት የሚወርድበት ወር ነውና፡፡ ፍጥረቱ ሆኖ ከእዝነቱ የተብቃቃ ማን አለና፡፡ በረመዳን ይበልጥ ወደ አላህ እንመለሳለን፡፡ የደረቀው ቀልባችንን እንዲርስ እንፈልጋለን፣  የረሕመቱ ወር በረከት ለኛም እንዲደርሰን እንከጅላለን፣ ለአላህ ባሮች የተከፈተው ሰፊ ችሮታው ለኛም ይደርሰን እንመኛለን፣ ለጥፋታችን ምህረቱን እንጠይቃለን፣ አላህ በዲኑ ላይ ያፀናን ዘንድ እንማፀነዋለን፡፡

በረመዳንም ሆነ በሌላ ጊዜ ወደ አላህ እንመለሳለን፣ አላህ (ሱ.ወ.) በከፈተልን የተውባ በር እንገባለን፣ የተሠጠንንም ዕድል እንጠቀምበታለን፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ያጣናቸውን ችሮታዎች ለማግኘት እንጓጋለን፣ ከአምላካችን ጋር እንታረቃለን፣ ፅናቱን ይለግሰን ዘንድ እንለምነዋለን፡፡ በወሩ ዉስጥ መልካሙን ነገር እንዳገራልን ከወሩ ዉጭም እንዲያገራልን እንማፀነዋለን፡፡

አላህ (ሱ.ወ.) ባሪያው በየትኛውም ጊዜ ስህተቱን አምኖ፣ በጥፋቱ ተፀፅቶ ወደርሱ በመጣ ጊዜ እስከዛሬ የት ነበርክ ብሎ አያባርርምና፣ እሱ ከወላጅ እናትም በላይ አዛኝ አምላክ ነውና ያለፍራቻና ይሉኝታ ወደ አላህ እንመለሳለን፡፡ ከረመዳን በፊት በተለያዩ ወንጀሎች ቆስለናልና፣ በሐራም ነገሮችም ብዙ ተበክለናልና ከቁስላችን መፈወስ እንፈልጋለን፣ ከህመማችን መዳን እንሻለን፡፡ ለዚህም የርሱ ችሮታ ያስፈልገናልና ወደርሱ እንመለሳለን፡፡

አላህ መመለሳችንን ይቀበለን፡፡ በተውበታችን ላይ ያፅናን፡፡ አሚን

 

 

SIMILAR ARTICLES