ንግድ እና ነጋዴነት

ንግድ እና ነጋዴነት

ንግድ እና ነጋዴነት

በተለይ በሀገራችን ሙስሊም ማኅበረሰብ በንግድ ሥራ ይታወቃል፡፡ በዚህ ርእስ ሥር ስለ ንግድ እና የነጋዴው ባህሪ ምን መምሠል እንደሚኖርበት ጥቂት ነጥቦችን አብረን ለማየት እንሞክራለን-

በኢስላም ማንኛውም ሐላል የሆነ ሥራ ሁሉ ክቡር ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ለመኖር በሚያደርገው ግብግብ ሥራን ተስፋው አድርጎ ከመንቀሣቀሱ በተጨማሪ ወደ ጥሩና መልካም ነገሮችም መሸጋገሪያዬ፤ ወደ ጌታዬም መቃረቢያዬ ነው ብሎ ካሰበ ምንዳ በሚያስገኝ የአምልኮ ተግባር ይተረጎምለታል፡፡

መሥራት ሀሳብን ይሰበስባል፣ ሰውን ከድህነት ያጠራል፣ የሌሎችን እጅ ከማየት ያብቃቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠንካራ አማኝ በዒባዳው ላይ ይበልጥ ሊበረታ የሚችለው የሠራና የበላ እንደሆነ ነው፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ የሱን ሐቅ ከተወጣን በኋላ ራሣችንን እንድናግዝና ለሥጋችንም ጊዜ እንዲኖረን አነሣስቶናል፡፡  ከቁርኣን የሚከተሉትን አንቀፆች እንይ፡-

‹ ሰላትም በተጠናቀቀች ጊዜ በምድር ውስጥ ተበተኑ፤ የአላህንም ችሮታ ፈልጉ፡፡ › (አል-ጁሙዓ ፡10)

‹እርሱ ያ ምድርን የተገራች ያደረገላችሁ ነው፡፡ በጋራዎችና በተራራዎችም ሂዱ፡፡ ከሲሣዩም ብሉ፡፡›( አል-ሙልክ፡15)

የአላህን ችሮታ ከምንፈልግባቸዉ መንገዶች መካከል ንግድ አንደኛዉ ነው፡፡ ሐቀኛና እውነተኛ ነጋዴ የተከበረና አላህ በሚወደው ሥራ ላይ ነው፡፡ ማህበረሰቡን እየጠቀመ ፤ ሀገርና ወገኑንም በመርዳት ላይ ነውና፡፡ ከኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ.) በተላለፈው ዘገባ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም

«خير الناس أنفعهم للناس» ‹በላጩ ሰው ለሰው ጠቃሚ የሆነ ሰው ነው፡፡› ብለዋል፡፡ (ጦበራኒ ዘግበውታል፡፡)

ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ከመላካቸው በፊት ከእናታችን እመት ኸዲጃ ረዲየሏሁ ዐንሃ ጋር የንግድ ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ እሷ ገንዘብ ያላትና የተከበረች የመካ እመቤት ነበረች፡፡ የነቢዩን እውነተኝነት፣ ታማኝነትና የመልካም ሥነምግባር ባለቤት  መሆናቸውን ባወቀች ጊዜ ወደ ሻም አገር ከአገልጋዩዋ ጋር ሄደው በገንዘቧ እንዲነግዱላት ጠየቀቻቸው፡፡ ነቢዩም ሰላለሁ ዐለይህ ወሰለም መይሰራ ከሚባል አገልጋይዋ ጋር በመሄድ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ በማግኘት ተመለሱ ፡፡ ይህ ታማኝነታቸው  ነበር ኸዲጃ ነቢዩን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ለጋብቻ እንድትጠይቃቸው ያነሣሣት፡፡

ነቢያችን ስንፍናን፣ ሥራ ፈትነትንና ተቀምጦ መብላትን እጅግ አድርገዉ ያወግዙ ነበር፡፡ በቡኻሪ ዘገባ

مَا أَكَلَ أَحَدٌ طَعَامًا قَطُّ خَيْرًا مِنْ أَنْ يَأْكُلَ مِنْ عَمَلِ يَدِهِ وَإِنَّ نَبِيَّ اللَّهِ دَاوُدَ عَلَيْهِ السَّلَام كَانَ يَأْكُلُ مِنْ عَمَلِ يَدِهِ 

‹አንድ ሰው በእጁ ሠርቶ ከሚያገኘው የተሻለ በላጭ ነገር አይበላም፡፡ የአላህ ነቢይ ዳዉድ (ዐ.ሰ.) እጃቸው ሠርተው ካገኙት ይበሉ ነበር፡፡› በማለት የሥራና የላብ ዉጤት ጣፋጭ መሆኑን ያስተምሩ ነበር፡፡ የነቢዩ ሰሐቦች ለሁለቱም ዓለም ታታሪ ሠራተኞች ነበሩ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም          لَأَنْ يَحْتَطِبَ أَحَدُكُمْ حُزْمَةً عَلَى ظَهْرِهِ خَيْرٌ لَهُ مِنْ أَنْ يَسْأَلَ أَحَدًا فَيُعْطِيَهُ أَوْ يَمْنَعَهُ

 

‹አንዳችሁ በጀርባው እንጨት ተሸክሞ ማምጣቱ ሰው ለምኖ ከሚሠጠው አሊያም ከሚከለክለው ይሻልለታል ፡፡› መክረዋቸዋልና፡፡ ከሰሐቦችም መካከል ምርጥ የሚባሉት እነ ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ እና ዑሥማን ኢብኑ ዐፋን ታላላቅ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡

ስለ ንግድ እና ነጋዴ አንዳንድ

ሐራም ነገርን መሸጥ

አንድ ነገር ሐራምነቱ የታወቀ ከሆነ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መልኩ መሸጥና ገንዘቡንም  መጠቀም ሐራም ነው፡፡  ያ ነገር የሚበላ ፣ የሚጠጣ፣ የሚለበስ ፣ የሚሠሩት ነገር አሊያም ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ሐራም ነገር መሸጡ የተከለከለ ስለመሆኑ ኢስላም ደንግጓል፡፡ መሸጡ ክልክል የሆነ ነገር ደግሞ ገንዘቡንም መዉሰድና መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡ ከሐራም  የሚገኝ ገቢን ለራስ መጠቀምም ሆነ ለሌላ አሣልፎ ስጦታ መስጠቱ አይበቃም፡፡  የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም

إن الله عز وجل إذا حرم أكل شيء حرم ثمنهُ. ‹ ኃሉና የተከበረው አላህ አንድን ነገር እርም ካደረገ ገንዘቡን እርም አድርጓል › ብለዋል፡፡ (አሕመድ እንደዘገቡት)

ከታማኙና እውነተኛው ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) በተላለፈው ዘገባ ‹የቂያማ ቀን የአንድ ባሪያ እግሮች አይንቀሳቀሱም ከአራት ነገሮች የተጠየቀ ቢሆን እንጂ፤ እድሜዉን በምን እንደጨረሠ፤ በእዉቀቱ ምን እንደሠራ፤ ሰውነቱን በምን ተግባር እንዳለቀ፣ ገንዘቡን ከየት እንዳገኘና ምን ላይ እንዳዋለ › የሚል ጥያቄ እንዳለብን ተነግሮናል ፡፡ እናም ከአሁኑ ለጥያቄዎቹ መልስ እናዘጋጅ፡፡ የመልሱንም ትክክለኛነነት እናረጋግጥ ፡፡ ልብ እንበል – ዛሬ ሥራ ነው ምርመራ የለም ፤ ነገ ደግሞ ምርመራ ነው ሥራ የለም ፡፡ በመሆኑም ስንሠራና ሀብት ስናፈራ በዘፈቀደ አንሰብስብ፤ ሐራም የገንዘብ ማግኛ መንገዶችን እንራቅ ፡፡

እያንዳንዱ ሐራም ነገር ዛሬ በባለቤቱ ላይ መጥፎ ጠባሳ አለው፤ የነገ ቅጣቱ ደግሞ የከፋ ነው፡፡ ሐራም የሚበላ የሚጠጣና በሐራም ያደገ በደለኛ ሰው ዱዓዑ ተቀባይነት የለውም፡፡  ዱዓዑ እንዲሰማለትና ምኞቱ እንዲሠምር የፈለገ የገንዘብ ምንጩ ከሐራም እንዳይሆን ተጠንቀቅ፡፡ በሐራም የተሠራች የዛሬዋ ትንሽ ነገር የነገውን ትልቅ ስኬት ልታሣጣ ትችላለችና ፡፡ ነቢያችን እንዲህ ይላሉ –

إن الله جميل يحب الجمال  ‹አላህ ቆንጆ ነዉ ቆንጆ ነገርን እንጂ አይቀበልም፡፡›

‹ከሐራም ያደገ ሰዉነት እሣት ለሱ በላጭ ነዉ፡፡› ይላሉ በሌላ ሐዲሣቸዉ ፡፡

መነፋፋቱንና ማደጉን አትዩ፡፡ በሐራም ያደገ ነገር ሁሉ ባዶና ውሸት ነው ጥንካሬ የለውም፡፡ መሠረቱም ደካማ ነው፡፡ ምሰሶውም ያረገረገ ነው፡፡ የሰዎችን በሐራም ነገሮች መወዳደር አይተን አንታለል፡፡ እነሱ እንደከበሩት ለመክበር ብለን መንገድ አንሣት፡፡ የነሱ አለመጠንቀቅ እኛን ከመጠንቀቅ አያግደን፡፡

يأتي على الناس زمان لا يبالي المرء ما أخذ منه، أمن الحلال أم الحرام

‹ በሰዎች ላይ ዘመን ይመጣል አንድ ሰው ገንዘቡ ከሐራም ይሁን ከሐላል የማይጨነቅበት› ብለዋል ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም፡፡ (ቡኻሪ እንደዘገቡት)፡፡ ዛሬ የምናየው ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉ ከዚህ የራቀ አይደለም፡፡›

ኢስላም ሐላል ነገሮች በግልፅ ደንግጓል፡፡ ሐራም ነገሮችንም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በመካከል ግን ሐላል ሐራምነታቸው በግልፅ ያልተለየ አጠራጣሪ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነሱን ከመዳፈር ይልቅ መፍራት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከመቅረብም ይልቅ መራቁ ነው ተመራጭ የሚሆነው፡፡ ሰሐቦች አንዲት ጉርሻ እንኳ ሐራም የበሉ እንደሆን እሷን ለማውጣት የማያደርጉት ጥረት የለም፡፡ ‹ለምን ከነፍሴ ጋርም አይሆንም አወጣታለሁ› ይሉ ነበር ታላቁ ሶሐባ አቡበክር አስስዲቅ ረ.ዐ. ፡፡

የሚያግራራን አላህ ያግራራለታል

አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ባሮቹን ሁሉ በፍትህና በመልካምነት አዟል፡፡ ፍትህ ደግሞ የስኬቶች ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ለነጋዴዎች ሲሆን ደግሞ ትልቁ ሀብት ነው፡፡ በንግድ ላይ እውነተኛነት፣ ፍትሃዊ መሆን፣ መጉዳትም ሆነ አለመጎዳት ፣ ለሰው ልጅ በጎ መዋልና ማግራራት ደግሞ ለራስ ደስታንና እርካታ ከአላህ (ሱ.ወ.) ዘንድ ደግሞ ዉዴታን ያጎናፅፋል፡፡ ማግራራት ሲባል በንግድ ወቅት ለአንድ እቃ ከተገቢው ዋጋ በላይ አለመጠየቅ፣ በቂ ገንዘብ የሌለውን ሰው አለማጨናነቅ ነው፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ዛሬም ሆነ ነገ ነገሮችን እንዲያገራለት የፈለገ ሰው አንድ ወንድሙ ‹የለኝምና ቀንስልኝ› ካለው ይቀንስለት፤ ጊዜ ስጠኝ ካለ ጊዜ ይስጠው፤ ተቸግሬያለሁ በዱቤ ስጠኝ ካለም ያግዘው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የገዛው እቃ ካልተመቸውና አልስማማው ካለ  መልስልኝ ብሎ ከጠየቀ ይመልስለት፣ ቀይርልኝ ካለም በመቀየር ይተባበረው፡፡ እናግራራ አላህ የሚያግራሩትን ይወዳልና፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡-

 رحم الله رجلا سمحا إذا باع وإذا اشترى وإذا اقتضى

‹ሲሸጥ፣ ሲገዛም ሆነ ሲፈርድ የሚያልፍ /የሚያግራራ/ የሆነን ሰው አላህ ይዘንለት› (ቡኻሪ እንደዘገቡት)

በሌላም ሐዲሣቸዉ  ‹የጨነቀውን ሰው ያገራለት አላህ የዱኒያና የአኪራ ጉዳዮችን ያገራለታል ፡፡› ብለዋል፡፡

በደልን እንጠንቀቅ

ትንሽ ይሁን ትልቅ ሰዎችን አላግባብ የምንጎዳበት እያንዳንዱ ነገር ሁሉ ዙልም /በደል/ ነው፡፡ በደል ደግሞ ዉጤቱ የከፋ ነው፡፡ በልብ፣ በቀብርም ሆነ በቂያማ ቀን ጨለማን ያወርሣል፡፡ ‹በደልን ፍሩ ፤ በደል የቂያማ ቀን ድርብርብ ጨለማ ነዉና› ይላሉ ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም፡፡

የቂያማ ቀን ጨለማ ነውና ማንኛዉም ሰው የተሟላ ብርሃንን ይፈልጋል፡፡ የዚያን ቀን ብርሃን ያላቸውና የሌላቸው ይኖራሉ፡፡ ያላቸው ሊኖራቸው የቻለው በዱኒያ ላይ ቆይታቸው ወቅት አላህን በመፍራታቸውና ከበደልም በመራቃቸው ነው፡፡  ዛሬ ገንዘቡ ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ የተወሠደበት ሰው ነገ ከወሠደበት ሰው በላይ አትራፊ እሱ ነው፡፡ ምክኒያቱም በነገው ቀን የፍርድ ዉሳኔ ገንዘብን በገንዘብ መመለስ ሣይሆን መልካም ሥራን ከበዳይ በመንጠቅና ለተበዳይ በመስጠት ነው የሚካሠው፡፡ ዕለተ ትንሳኤ ገንዘብ ሳይሆን መልካም ሥራ የሚያስፈልገበት አደባባይ ነው፡፡

ለኛ እጅጉን አዛኝ የሆኑት ነቢያችን እንዲህ በማለት ይመክሩናል

من كانت عنده مظلمة لأخيه فليتحلل منها، فإنه لا دينار ولا درهم من قبل أن يأخذ لأخيه من حسناته، فإن لم يكن له حسنات أخذ من سيئات أخيه فطرحت عليه“.

‹ወንድሙን የበደለ ሰው ዲናርም ሆነ ድርሃም የሌለበት ቀን ከመምጣቱና መልካም ሥራዉ ተወስዶ መልካም ሥራ ከሌለውም የወንድሙ መጥፎ ሥራ በሱ ላይ የሚጫንበት ቀን ከመምጣቱ በፊት በደሉን ዛሬዉኑ ይካስ፡፡› (ቡኻሪ ዘግበውታል)

የነገዉን ከባድ ፈተና ለማለፍና ጀነት ለመግባት ገንዘብ ሣይሆን ከምንም በላይ መልካም ሥራዎች ያስፈልጉናል፡፡ ዛሬ የምናገኘው ተራ ጥቅም ነገ ከሚወሰድብን በምንም መልኩ የተሻለ አይሆንም ፡፡

ማታለልና ማጭበርበር

አንድ ቀን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም  ለምግብ በሚውልና በሚሸጥ (ክምር) እህል ዘንድ አለፉ፡፡ እጃቸዉንም ወደ ክምሩ በሰደዱ ጊዜ በዉስጡ እርጥበት አገኙ ‹ ይህ ምንድነዉ የዚህ እህል  ባለቤት ሆይ !› በማለት ጠየቁ፡፡ ‹ዝናብ አግኝቶት ነው› አለ የእህሉ ባለቤት፡፡ ‹ ታዲያ ሰዎች እንዲያዩት ለምን እላዩ ላይ አላደረግክም ?› አሉት፡፡ በመቀጠልም ‹ ያታለለን ከኛ አይደለም ፡፡› በማለት ተናገሩ ፡፡

እነኚህንና የመሣሠሉት ዓይነት ማታለሎች ዛሬ በማህበረሰባችን ዉስጥ በዝተዋል፡፡ ኦሪጅናል  ያልሆነዉን እቃ ነው ብሎ ለማሣመን መሞከር፣ ዐይብ እንዳለበት እያወቁ ሸፋፍኖ መሸጥ፣  ሁለተኛውን ደረጃ ዕቃ አንደኛ ነው በማለት መዋሸት እነኚህ ሁሉ ከማታለል የሚመደቡ ናቸው፡፡

በየትኛውም መልኩ ሰዎችን ማታለልን ሸሪዓችን አይደግፈውም፡፡ ሰዎችን በማምታታት የሚገኘው ገንዘብ የቱን ያህል ቢቆለልም አንድ ቀን መናዱ አይቀርም፡፡  ስለዚህ ለጥቂት ዓለማዊ ጥቅሞች ብለህ ከጌታችን አንጣላ፡፡ ደግሞም አንዋሽ፤ ዉሸት እጅግ የተጠላ ባህሪ ነውና ‹ ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው፤ አይዋሸውም፡፡› ብለዋል ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዉሸት የንፍቅና ምልክት ነዉ ፡፡ ወንድምህ እያመነህ አንተ የምትዋሸዉ ከሆነ ትልቅ ክህደት ነው፡፡ እዉነትን እያወቁ መደበቅ ፤ ለሌሎች አለማሰብ ፣ ስግብግብነትና የራስን ጥቅም ብቻ ከማሣደድ የሚመነጭ ነው፡፡ ቢጎዳንም እዉነትን እንናገር፣ ቢጠቅመንም ዉሸትን እንተው፡፡ እቃችን የሌላትን ጥራት አላት አንበል ፣ ጉድለቷን አንደብቅ ፤ ነዉሯን አንሸፋፍን ፤ እንከኗን አናለባብስ ፡፡ ያኔ አላህ ንግዳችንን ይባርክልናል፤ እውነትን በመናገራችን ይክሰናል፡፡ የአላህ ነቢይ እንዲህ ብለዋል

‹ ገዥና ሻጭ እስካልተለያዩ ድረስ (መሻሻጣቸዉን የማፍረስም ሆነ የማፅደቅ) ምርጫ አላቸዉ ፡፡ እውነትን የተናገሩና ሁሉን ነገር ግልፅ ያደረጉ እንደሆነ መሻሻጣቸዉ /መገበያያታቸዉ/ ይባረክላቸዋል ፡፡ የደበቁና የዋሹ እንደሆነ ግን የግብይታቸዉ በረከት ይነሣል፡፡›

ሥፍርና ሚዛን ማጉደል ሌላው ሰዎችን የማታለያ መንገድ ነው፡፡ ይህም ሆነ ብሎ አሊያም በቸልተኝነት ‹ምንም አይደል፣ ብዙም ለዉጥ የለዉም › በማለት ሊሆን ይችላል ፡፡ ሐራም ነገር ትንሽ ቢሆንም ሐራምነቱን አይለቅም ፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ በብዙ የቁርኣን አንቀፆች ላይ ከዚህ ዓይነቱ እኩይ ድርጊት አስጠንቅቋል ፡፡ ወይሉን ሊልሙጠፍፊን / ለሰላቢዎች ወየዉላቸው፣ እነዚያ › ( አል-ሙጠፍፊን ፡1-3) የሚለው አንዱ ነው፡፡ በሌላ አንቀጽም

‹ ስፍርን ሙሉ ከአክሳሪዎችም አትሁኑ ፤ በትክክለኛው ሚዛንም መዝኑ፤ ሰዎችንም ነገሮቻቸዉን አታጉድሉባቸው፤ በምድርም ላይ አጥፊዎች ሆናችሁ አታበላሹ ፡፡ › ( ሹዐራእ ፡  181-183 )

ከላይ በተገለፁት አንቀፆች አላህ ለነዚያ ለራሣቸዉ ሲሰፍሩ የሚሞሉትን ለሌሎች ሲሰፍሩ የሚያጎድሉትን አስጠንቅቋል ፡፡ ታላቁን ቀን አይፈሩም እንዴ ! ሲልም ይጠይቃል ፡፡  ሁለት ነገሮችን ልብ እንበል-

አንደኛ – አንድ ሰው የእቃዉን ምንነት መደበቁ ፤ ኦሪጅናል ያልሆነዉን ነው ማለቱ ፤ የሌላትን መናገሩና ቃላትን ማሠማመሩ፤ ሥፍርም ሆነ ሚዛን ማጉደሉ ቀድሞ በተፃፈው ርዝቁ ላይ ምንም አይጨምርለትም ባይሆን ድፍርስ ውሃ ከንፁህ ጋር ሲቀላቀል እንደሚያደፈርሰው ሁሉ ሐላል ከሆነው ሀብቱ ጋር ሲቀላቀል ያጠፋዋል በረከትን ይነሣዋል፡፡ ሰደቃ ከገንዘብ እንደማያጎድል ሁሉ ክህደትና ማታለልም በገንዘብ ላይ አንዳች ነገር አይጨምሩም፡፡

2ኛ- የአኺራ ትርፍ ከዱኒያዉ እጅግ የተሻለ መሆኑን አንዘንጋ ፡፡ የዚህች ዓለም ጥቅም የሰው ልጅ እድሜ ከፍ ባለ ቁጥር ይቀንሣል ፤ በደሏና ጥፋቷ ፤ ሀጢአትና ወንጀሏ ግን ሸክም በመሆን አብሮ አኺራ ይወርዳል፡፡ ታዲያ ዐቅለኛ የሆነ ሰው ትንሹን ነገር ከትልቁ፣ ተራውን ነገር ከበላጩ እንዴት ይመርጣል ያስቀድማል ፡፡

መሀላችሁን ጠብቁ

የአል-ማኢዳህ ምዕራፍ ቁ -93 ላይ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ‹ መሃላችሁን ጠብቁ › ይለናል፡፡ መማል የግድ ካልሆነ በስተቀር ለመማል ብቻ መማል ተገቢ አይደለም፡፡ ዛሬ ለትንሹም ሆነ ለትልቁ ነገር መሐላ የተለመደ ሆኖ እናያለን ፡፡ በመሀላ አለመጠንቀቅ ለአላህ ሥም  ክብር አለመስጠት ነው፡፡ አንድን ነገር ለመሸጥ መሀላ የግድ መሆን የለበትም ፡፡ ሙስሊም ሻጭ እውነትን መናገር ገዥውም ሻጭን ማመን ግድ ይለዋል ፡፡  አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ በውሸት በስሙ የሚነግድን ሰው ከባድ የሆነ ዛቻ አዉርዶበታል ፡፡ አሊ ዒምራን  77 ፡፡

የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም በሐዲሣቸዉ እንዲህ ብለዋል ‹ የቂያማ ቀን አላህ ሦስት ዓይነት ሰዎችን አያናግራቸውም ፤ ወደነርሱም አይመለከትም ፤ ከመጥፎ ወንጀላቸውም አያጠራቸውም ፤ ለነሱም አሣማሚ ቅጣት አለ› ይህንኑ ሦስት ጊዜ ደጋግመው ተናገሩ ፡፡ አቡዘርም ረዲየሏሁ ዐንሁ ‹ ባዶ ሆኑ ከሠሩ፤ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እነሱ እነማናቸው › በማለት ጠየቀ ፡፡ እርሣቸውም ‹ ልብሱን መሬት ላይ የሚጎትት፣ ጉረኛ / በሠጠዉ ነገር የሚመፃደቅ/ ፣ በውሸት መሃላ እቃውን የሚሸጥ › በማለት መለሱ ፡፡

በሌላም ሐዲሣቸው   (الحلف منفقة للسلعة، ممحقة للبركة)) ‹መሐላ እቃን ያስገኛል፤ በረከትን ግን ያጠፋል፡፡› ብለዋል ፡፡

መጨራረት

ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው፣ በምንም መልኩ አይበድለውም፣ ሊበድለውም አይገባም፡፡ ከወንድማማችነት ሐቆች መካከል አንድ ሙስሊም ለራሱ የሚወደውን መልካም ነገር ለወንድሙ መውደዱ ነው፡፡  የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ‹ ወደ ገበያ የሚመጡትን (ነጋዴዎች) መንገድ ላይ አትጠብቁ፡፡ አንዳችሁም በሌላኛው ገበያ ለይ አይሽጥ፡፡›

አንዱ በሌላኛዉ ገበያ ላይ መሸጥ ማለት- አንደኛው ሊሸጥ በመደራደር ላይ እያለ ሌላኛዉ አይጥራው፣ ታልቃ አይግባ፣ ከሸጠ በኋላም ቢሆን እኔ ከሱ ባነሠ ዋጋ እሸጥልሃለሁ በማለትና በመሣሠሉት ቃላት ሀሳቡን አያስለውጠው ማለትን ያካትታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ነጋዴዎች የሀገሬውን ዋጋ የማያውቅን ሰዉ በርካሽ ዋጋ ለመግዛት ብለዉ ቀድመው መንገድ ላይ በመውጣት እንዳይገዙት ያሣስባሉ፡፡ ለመግዛት ሀሳቡ ሣይኖር በእቃ ላይ ዋጋ ጨምሮ ሌላውን ማሣሳትም ሌላኛው ስህተት ነዉ ፡፡

የሰላት ነገር

ሰላት በኢስላም ውስጥ ታላቅ ቦታ አላት፡፡  ከአምስቱ የእስልምና ማእዘናት አንዷ ስትሆን የሃይማኖቱም ምሠሦ ናት፡፡ ይህ ከመሆኑ ጋር በንግድ ምክኒያት የሰላትን ነገር ችላ የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ዱኒያዊና ዲናዊ ነገሮች አንድ ላይ የመጡ እንደሆን ሁሌም የዲን ጉዳይ ይቀድማል፡፡ ምክኒያቱም ዱኒያ ጠፊና ጊዜያዊ ስትሆን አኺራ ደግሞ ዘላለማዊና ቋሚ አገር ናትና፡፡

አላህ በአኺራ ያዘጋጀለትን ድግስ በወጉ የተገነዘበ በዚህኛው ዓለም ጥቅም አይታለልም፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ በንግድና በሌላም ምክኒያት ከሰላት የማይዘናጉት ትጉሃን ባሮቹን ያሞካሻል፡፡ (ሱረቱ ኑር  36- 37) ፡፡

ምእመናን ከሥራ አልተከለከሉም፡፡ ይሸጣሉ ይገዛሉ፤ ነገር ግን አላህ ግዴታ ያደረገባቸው ነገር የመጣ እንደሆን ከሱ የሚያስቀድሙት ነገር የለም፡፡ ሰሐቦች ሰላት ሲደርስ አሊያም ሙአዚኑ ወደ መስጊድ የተጣራ እንደሆን ትርፉ የቱን ያህል የበዛ ቢሆን እንኳ የሱቃቸውን በር ይዘጋሉ፡፡ እኛም የነዚያን ደጋጎች ፈለግ እንከተል፡፡ በአላህ (ሱ.ወ.) በመተማመን ወደ መስጊድ እንምጣ፡፡ ርዝቃችን የትም እንደማያመልጥ እርግጠኛ እንሁን፡፡ ከአምልኮ ተግባራት ሁሉ ከግዴታ ነገሮች በላይ ወደ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ የሚያቀርብ ምንም የለም፡፡ ሰላት ዋጋዋ ከባድ ነው፡፡ በቂያማ ቀን የሰው ልጅ መጀመሪያ የሚጠየቀው ከሷ ነው፡፡ እሷ ካማረች ሁሉም ነገር ያምራል ከተበላሸች ደግሞ ዉድቀት ይበዛል – አላህ ይጠብቀን ፡፡ አምላኩ ግዴታ ያደረገበትን የተወጣ ሰው ትርፉ የበዛ ነው፡፡ መንፈሱ ይረካል ፣ ዉስጡ ይሰክናል ፣ ደረቱ ይሠፋል ፡፡ ወደ መስጊድ ስንገባ ‹ ጌታዬ ሆይ ! የእዝነትህን በር ክፈትልኝ› ስንወጣ ደግሞ‹ ጌታይ ሆይ ! ከችሮታህ እለምንሃለሁ› የማለታችን ሚስጢሩ ምን ይሆን!፡፡

በራእ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ.) የጁሙዓ ሰላት ከሰገደ በኋላ በመስጊድ በር ላይ ይቆምና ‹ጌታዬ ሆይ ! ጥሪህን ተቀብዬ መጥቻለሁኝ ፤ ግዴታ ያደረግክብኝንም ሰላት ሰግጃለሁ ፤ እንዳዘዝከኝ በምድርህ ላይ ተበተንኩ፤ አንተ በላጩ ለጋሽ ነህና ከችሮታህ ለግሠኝ ፡፡› ይል ነበር ፡፡

አላህ ለሚወደው ነገር ሁሉ ይወፍቀን፡፡

WWW.ALIFRADIO.COM