አላህ ጥሩ ነውና ጥሩን ነገር እንጂ አይቀበልም…

0
388

تَعَالىَ طَيَّبٌ لايَقْبَلُ إلاَّ طَيَّبَّا،  وإنَّ الله أَمَرَ الُمؤْمِنينَ بمَا أَمَرَبهِ المُرْسَلينِ فقاَلَ تَعَالَى (يَا أَيُّها الرُّسُلُ كُلُوا مِنَ الطَّيَّبَاتِ واعْمَلُوا صَاِلحاً) وقَالَ تَعَالَى (يَاأَيُّها الَّذِينَ آمَنُوا كُلُوا مِنْ طَيَّبَاتِ مَارَزَقْنَاكُمْ) ثُمَّ ذَكَرَ الرَّجُلَ يُطِيلُ السَّفَرَ أَشْعَثَ أَغْبَرَ يَمُدُّ يَدَيِه إلى السَّمَاءِ : يَارَبُّ يَارَبُّ، ومَطْعَمُهُ حَرَامٌ ومَشْرَبُهُ حَرَامٌ ومَلْبَسَهُ حَرَامٌ وغُذِىَ بالْحَرام فَأَنىَّ بُسْتَجَابُ لَه. رَوَاهُ مُسْلِمٌ

 

ከአቢ ሁረይራ (ረ.ዐ) የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋል፡-

‹ልዑል የሆነው አላህ ጥሩ ነውና ጥሩን ነገር እንጂ አይቀበልም፡፡ አላህ መልዕክተኞችን ባዘዘበት ነገር ምእመናንንም አዟል፡፡ ልዑል የሆነው አላህ እንዲህ ብሏል ‹እናንተ መልዕክተኞች ሆይ! ከጥሩ ነገሮች ብሉ፣ በጐ ሥራንም ሥሩ…» (አል-ሙእምኑን፡ ቁ-51) እንዲሁም «እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከነዚያ ከሰጠናችሁ ጣፋጮች ብሉ…» (አል-በቀረህ ቁ፡ 172) ፡፡ ከዚያም ስለአንድ በረጅም ጉዞ ላይ ያለ፣ ፀጉሩ የተንጨበረረና በአቧራ የተሸፈነ ሰው አወሱ፡፡ እጁን ወደ ሰማይ ዘርግቶ ጌታዬ ሆይ! ጌታዬ ሆይ! ይላል፡፡ የሚመገበው ሐራም፣ የሚጠጣው ሐራም፣ የሚለብሰው ሐራም፣  ያደገውም በሐራም ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ዱዓው ተቀባይነት ያገኛል? ሲሉ ተናገሩ፡፡›   (ሙስሊም ዘግበውታል፡፡)

አምላካችን አላህ (ሱ.ወ.) በምሉእነት ባህሪው ብቻ የሚገለጽ ከጉድለት ሁሉ የጠራ ፍፁም የሆነ አምላክ ማለት ነው፡፡ በሁሉ ነገሩ እንከን አልባ የሆነ ጌታ ነው፡፡ ጥሩነት መገለጫው ነው፤ ቆንጆ እና ዉብ ነገር ሁሉ የሚገባው ለርሱ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ከሰው ልጆችም ንፁህ እና ፅዱ ነገሮችን ብቻ ይቀበላል፡፡ የተበላሸና መጥፎ ነገርን አይቀበልም፡፡ በሌብነት፣ በማምታትም ሆነ በወንጀል የተገኘን ምንጩ ሐራም የሆነን ነገር አይቀበልም፡፡ ማንኛውም ሥራችን አላህ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ለሱ ብቻ ታስቦ የተሠራ መሆን አለበት፡፡ የተፈቀደና መልካም ነገርም መሆን አለበት፡፡

አላህ (ሱ.ወ.) አማኞች ሁሉ ጥሩ ነገር እንዲበሉና ጥሩ ነገርም እንዲሠሩ አዟል፡፡ ይህም እስልምና በአካልም ሆነ በመንፈስ ንፅህና ጥራት ላይ ምን ያህል እንደሚያተኩር ያሳያል፡፡ ስለሆነም የዕለት ተዕለት ሥራችን፣ ዉሎአችን፣ ሶላታችን፣ ፆማችን፣ ዱዓኣችን ሁሉ ጥራት ያለው መሆን አለበት፡፡ ባጠቃላይ ለአላህ ብለን የምንሠራቸው የአምልኮ ተግባራት በሙሉ በጥራት የተሞሉ መሆን አለባቸው፡፡ በሱ ከማጋራት የፀዱ፣ ከፈጠራና አልባሌ ከሆኑ አመለካከቶች የጠሩ መሆን አለባቸው፡፡ አላህ ጥሩ ነገርን እንጂ አይቀበልምና፡፡

በተለይ በዚህ ሐላል ነገር ውድ በሆነበት ዘመን ስለ ዱዓችን ምላሽ ማጣት ስናስብ ስለ የሲሳያችን ምንጭ ሐላል ይሁን ሐራም ማጣራትና ራሣችንን መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ የሰው ልጅ ልመናውና ተማፅኖው አላህ ዘንድ ተሰሚነት ይኖረው ዘንድ ለገቢ ምንጩ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ዱዓእን ተቀባይነት ከሚያሳጡ ነገሮች መካከል የአንድ ሰው የሲሳይ ምንጩ ከሐራም ነገር መሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው ምግቡ፣ መጠጡም ሆነ የገቢ ምንጩ ሐራም ሆኖ ሳለ በጉስቅልና ዉስጥ ጭምር ሆኖ ጩኸቱን ወደ አላህ ቢያሰማ አላህ አይሰማውም፡፡ እናም በዚህ ዙሪያ በእጅጉ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ይህ ሐዲሥ ያሳስባል፡፡

www.alifradio.com