አንድ ሙስሊም ወንድም በሌላኛው ሙስሊም ላይ ያለው ሐቆች –

0
4433

muslim-greetings1ሙስሊም በሙስሊም ወንድሙ ላይ ሐቅ አለው፡፡ ይህንን ሐቅ መወጣት በማንኛውም ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው፡፡ በተለያዩ ነቢያዊ ሐዲሦች ዉስጥ ከተነገሩ አንድ ሙስሊም በሌላኛው ላይ ካለው ሐቆች /መብቶች/ መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-

 • ሰላምታን ማቅረብ /አሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላህ ወበረካቱህ ማለት/ አንድ ሙስሊም ሙስሊም ወንድሙን በሚያገኝበት ጊዜ ቢያውቀውም ባያውቀውም ሰላምታ ሊያቀርብለት ይገባል፡፡ በሰላምታ መቅደምም ተወዳጅ ድርጊት ነው፡፡
 • ሰላምታን መመለስ – ሰላምታ የቀረበለት ሰው ደግሞ ሰላምታውን በተመሳሳይ አሊያም በተሻለ መልኩ መመለስ ይኖርበታል፡፡ ሰላምታ መመለስ ግዴታ ነው፡፡
 • ያስነጠሰን ማስደሠት (የርሐምከላህ ማለት) – ማስነጠስ ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ ከጭንቀት በኋላ ርግበት፡፡ ስለሆነም ሙስሊም በዚህን ጊዜ ጌታውን ያመሰግናል፡፡ አልሐምዱ ሊላህ በማለት፡፡ አጠገቡ ያለ ሙስሊም በዚህ ሊደሰትለትና የርሐምከላህ (አላህ ይዘንልህ) ሊለው ይገባል፡፡
 • የታመመን መጠየቅ – የታመመ ሰው መጠየቅ አለበት፡፡ ሙስሊም ሲታመም ወንድሞቹ ሊጎበኙት፣ በፈውስ እና በአላህ እዝነት ሊያበረታቱት እና ዱዓእ ሊያደርጉለት ይገባል፡፡
 • ለጥሪው ምላሽ መስጠት – አንድ ሙስሊም ሰርግ፣ ሰደቃ አሊያም ሌላ የደስታም ይሁን ሌላ ዝግጅት ኖሮት በዝግጅቱ ላይ እንድንገኝለት የጋበዘን እንደሆነ መገኘት ግድ ነው፡፡
 • የሞተ እንደሆነ ጀናዛውን መከተል /ወደ መቃብር መሸኘት – መቃብር ወደመጨረሻው ዓለም መሸጋገሪያ ሥፍራ ነው፡፡ የሞተ ሰው ምድር ላይ ያሳለፈውን ሥራ ይዞ አላህ (ሱ.ወ.) ፊት ይቀርባል፡፡ ስለሆነም ሙስሊሞች ወንድማቸው የሞተ እንደሆነ አጥበው፣ ከፍነውና ሰግደውበት የአላህን (ሱ.ወ.) እዝነትና ምህረትም ለምነውለት ወደማይቀረው ቤቱ ሊሸኙት ይገባል፡፡
 • የማለን መሀላውን ማፅናት – አንድ ሙስሊም ያደርግልኛል ብሎ በኛ ተማምኖ የማለ እንደሆነ ልናሳፍረው አይገባውም፡፡ መሀላውን ልናፀናለት ይገባል፡፡
 • የተበደለን ማገዝ – አንድ ሙስሊም የተበደለ እንደሆነ በቻልነው ሁሉ ከጎኑ መቆም ይኖርብናል፡፡ ይህም እሱ ከኛ ላይ ያለው አንድ መብቱ ነው፡፡ የበደለ እንደሆነም እንዳይበድል ልናስታግሰው ይገባል፡፡
 • የቸገረውን ሰው ከችግሩ ለማውጣት መረባረብ፣ የተጨነቀንም ከጭንቀቱ መገላገል፡፡ ሙስሊምን ከጭንቀቱና ከችግሩ የገላገለን ሰው አላህ በቂያማ ቀን ከችግር እንደሚገላግለው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ተናግረዋል፡፡
 • ምክር ለሚያስፈልገው ሰው ማማከር – ሙስሊም ወንድማችን ያማከረን እንደሆነም ልናማክረው ግድ ይላል፣ ያሳሰበው ነገር ካለም መላ ልንፈልግለት ይኖርብናል፡፡
 • ያጠፋን ነውሩን መሸፈን – አንድ ሙስሊም ያጠፋ እንደሆነ ጥፋቱን አደባባይ ማውጣትና ማዋረድ ተገቢ አይደለም፡፡ ገመናውን ልንሸፍንለትና በሚስጢር ልንመክረው ይገባል፡፡
 • ሙስሊም አለመናቅ – አላህ መልዕክተኛ ለአንድ ሰው ክፋቱ ሙስሊም ወንድሙን መናቅ በቂ ነው፡፡› ብለዋል፡፡ አንድ ሙስሊም በአላህ በማመኑ ብቻ ትልቅ ክብር አለው፡፡
 • ከዚህም ሌላ ሙስሊም በሙስሊም ወንድሙ መቅናትና መመቅኘት የለበትም፡፡ በደል፣ ጥላቻና ኩርፊያንም ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ ከሶስት ቀን በላይም ሊያኮርፈው አይገባም፡፡ በመልካም ነገርና በአላህ ፍራቻም ሊያስታውሰው ይገባል፡፡ እነኚህና የመሳሰሉት ሁሉ በአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሐዲሥ የተጠቀሱ ሐቆች /መብቶች/ ናቸው፡፡

www.alifradio.com