የረጀብ ወር ትርክቶች

0
5813

የረጀብ ወር ትርክቶች

አላህ (ሱ.ወ.) ሰውን ከሰው፣ ቦታን ከቦታ፣ ጊዜን ከጊዜ አበላልጧል፡፡ ይህንንም ያደረገበት የራሱ የሆነ ጥበብና ሚስጢር አለው፡፡ ጥበብና ሚስጢሩን ልናውቅም ላናውቅም እንችላለን፡፡ ከምናውቃቸው ጥበቦች መካከል የጊዜያትን ብልጫ ተገንዝበን በዕድሉ በመጠቀም በነርሱ ዉስጥ እንድንጠቀምና ይበልጥ ወደ አምላካችን እንድንቃረብበት ዘንድ ነው፡፡ ለምሳሌ ከወራት መካከል ረመዳን ትልቅ ትሩፋት ያለው ወር ነው፡፡ ረመዳን ዉስጥ የሚሠሩ አምልኮዎች በሌሎቹ ወራት ዉስጥ ከሚሠሩት በተለየ ሁኔታ ምንዳቸው ተነባብሮ ይከፈለናል፡፡ በወሩ ዉስጥ ከሺህ ቀናት የምትበልጥ አንዲት ሌሊት አለች፤ እሷን መጠቀም መቻል ትልቅ ትርፍ ነው፡፡ ከሳምንቱ ቀናት ዉስጥም ጁሙዓ ትልቅ ቀን ነው፡፡ በዉስጧ ሳዐት አልኢጃባ የምትባል አላህ ዱዓእን የሚሰማበት ጊዜ አለች፡፡

በዓመት ዉስጥ አሥራ ሁለት ወራት አሉ፡፡ ከአሥራ ሁለቱ ወራት ዉስጥ አራቱ የተከበሩ ወራት ናቸው፡፡ ረጀብ፣ ዙል-ቂዕዳ፣ ዙል-ሒጃ እና ሙሐረም ይሠናሉ፡፡ በነኚህ  ወራት ዉስጥ የአላህን ድንጋጌዎች በመጣስ ራሣችንን እንዳንበድል አላህ (ሱ.ወ.) መክሮናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ይላል፡-

‹የወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ዉስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን አሥራ ሁለት ወር ነው፤ ከነርሱ ዉስጥ አራቱ የተከበሩ ናቸው፡፡ ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው፤ በነርሱ ዉስጥም ነፍሶቻችሁን አትበድሉ፡፡….›› (አት-ተውባ ፡ 36)

ቡኻሪና ሙስሊም ባስተላለፉት ዘገባ ነቢዩም ሰ.ዐ.ወ. በሐዲሣቸው ስለነኚህ ወራት ክቡርነት መስክረዋል፡፡ ይዘነው ያለው የረጀብ ወር አላህ (ሱ.ወ.) ክብር ከሠጣቸው አራቱ ወራቶች መካከል አንዱ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ከዚህ ዉጭ ስለ ረጀብ ወር ብልጫና ልዩነት በቁርኣንም ሆነ በሶሒሕ ሐዲሥ የተላለፈ ልዩ መልዕክት የለም፡፡

ሆኖምግን የረጀብ ወር ሌሎች ተጨማሪ ትሩፋቶች እንዳለው በሰፊው ሲነገር እንሰማለን፡፡ በዚሁ መነሻነትም ብዙዎች የረጀብን ወር ሙሉዉን አሊያም አብዛኛውን የወሩን ክፍል ሲፆሙ እንዲሁም ሌሎች ወደ አላህ ያቃርበናል ብለው የሚያስቡትን በርካታ ተግባራትን ለምሳሌ እርድ፣ ሶለዋት፣ ኢዕቲካፍ፣ ዑምራ፣ ሰደቃና የመሳሰሉትን በተለየ መልኩ ሲፈጽሙ እናያለን፡፡

እርግጥ ነው ስለ ረጀብ ወር ትሩፋት  ብዙ ዘገባዎች ተላልፈዋል፡፡ ሆኖምግን የሐዲሥ አጥኚ ሊቃዉንቶችና ዑለሞች እንዳሉት እነኚህን በረጀብ ወር ዙሪያ የተነገሩ መልዕክቶች  አንድም ደካማ አሊያም ዉድቅ ዘገባዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ተቀባይነት የላቸውም፡፡

ታላቁ ዓሊም አልሓፊዝ ኢብኑ ሐጀር ረሒመሁላህ እንደሚሉት – በረጀብ ወር ታላቅነት እና ከሱ የተወሰኑ ቀናትን በመፆሙ፣ አሊያም የተወሰኑ ሌሊቶችን በመቆሙ ዙሪ ለማስረጃ የሚሆን አንድም የተላለፈ ጠንካራ ሐዲሥ የለም፡፡ በርካታ ሐዲሦች የመጡ ቢሆንም ደካማና ዉድቅ ናቸው፡፡›[1] ብለዋል፡፡

በረጀብ ወር ዉስጥ ተከስተዋል ከሚባሉ ክስተቶች መካከል አንዱ ኢስራእ እና ሚዕራጅ (የአላህ መልዕክተኛ ሰ.ዐ.ወ. ወደ ሰማዩ ዓለም ያደረጉት ጉዞ) ነው፡፡ ይህ ቀን የሚውለው በረጀብ ሀያ ሰባተኛው ላይ ቀን ላይ እንደሆነ ብዙ አፈታሪኮችን እንሠማለን፡፡ በርግጥም የኢስራእ እና ሚዕራጅ ሌሊት በእስልምና ዉስጥ ትልቅ ቦታ የሚሠጠው ታሪካዊ ሌሊት ስለመሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖምግን ይህ ቀን የዋለው በተጠቀሰው ወርና ቀን ዉስጥ ስለመሆኑ ተኣማኒነት ባላቸው ሐዲሦች የተላለፈ ዘገባም የለም፡፡  ቀኑንም በፆም እና በዒባዳ አሳልፉ ተብሎ የተነገረ ልዩ መልዕክት የለም፡፡ ከኛ ወደ መልካም ነገር በመሽቀዳደም የሚታወቁት ቀደምት ኸሊፋዎችም ሆኑ ሶሐቦችና ታቢዒዮች አላደረጉትም፡፡

አልሓፊዝ ኢብኑ ሐጀር ፈትሑልባሪ በተሠኘው ኪታባቸው ዉስጥ ‹ኢስራእና ሚዕራጅ ስለተከናወነበት ወር ከአሥር በላይ አባባሎች ተገኝተዋል፣ ከነኚህም መካከል በረመዳን፣ በሸዋል፣ በረጀብ፣ በረቢዕ አልአወል እንዲሁም በረቢዕ አልኣኪር ያሉ አሉ፡፡[2] ብለዋል፡፡

ሸይኽ ኢብኑ ተይሚያ ረሒመሁላህ እንደሚሉት – ኢስራእ እና ሚዕራጅ በየትኛው ወር ዉስጥ እንደተደረገ የሚታወቅ መረጃ የለም፡፡›[3]

ስለ ፆም ጉዳይ ከተነሳ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) ከረመዳን ቀጥሎ በብዛት የሚፆሙት የሸዕባንን ወር እንደሆነ ሶሒሕ ዘገባዎች ተላልፈዋል፡፡ በቡኻሪና ሙስሊም በተላለፈው ዘገባ  እናታችንዓኢሻ  ረ.ዐ. እንዲህ ብለዋል –  የአላህ መልዕክተኛ የረመዳንን ወር እንጂ የትኛውንም ወር ሙሉውን ፆመው አያውቁም፡፡ አብዛኛውን ጊዜዉን የሚፆሙት ደግሞ የሸዕባንን ወር ነው፡፡›

ከኡሳማ ኢብኑ ዘይድ ረ.ዐ እንደተወራው ደግሞ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከሌሎች ወራቶች በበለጠ ሸዕባንን በብዛት ሲፆሙ አያለሁ አልኳቸው፡፡› አለ፡፡ እርሣቸውም  ‹(ሸዕባን) ሰዎች በረጀብ እና በረመዳን መካከል ሰዎች የሚዘናጉበት ወር ነው፡፡ ሥራዎች ወደ ዓለማቱ ጌታ ከፍ የሚደረጉበት ወርም ነው፡፡ ስለሆነም ፆመኛ ሆኜ ሥራዬ ከፍ እንዲል (እንዲቀርብ) እፈልጋለሁ፡፡ አሉኝ፡፡ ብለዋል፡፡ ሐዲሡን አቡ ዳዉድ፣ ነሳኢ እና ኢብኑ ኹዘይማ ዘግበውታል፡፡

ስለሆነም ከዚሁ በመነሳት ስለ ረጀብ ወር የተላለፉ ዘገባዎችም ሆነ ዘገባዎቹ መሠረት በማድረግ የሚፈፀሙ የተለያዩ የአምልኮ ተግባራት የእስልምና አስተምህሮ እንዳልሆኑ አውቀን መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ አንድን የአምልኮ ተግባር ለመፈፀም ስንነሳሳም ግልጽ የሆኑ የሸሪዓዉን አስተምህሮዎችና ተኣማኒነት ያላቸውን ዘገባዎች መሠረት ልናደርግ ይገባል፡፡ ካልሆነ በሃይማኖት ዉስጥ ዉድቅ እና የጥመት መንገድ በሆነው ቢድዓ ላይ ልንወድቅ እንችላለንና፡፡

[1]   تبيين العجب فيما ورد في فضل رجب ، لابن حجر

[2]    ابن حجر   فتح الباري ((7/242 243) الخلاف في وقت المعراج

[3] زاد المعاد لابن القيم ، 1/275

#በአሊፍ ራዲዮ #