የደም ጉዳይ

የደም ጉዳይ

የደም ጉዳይ

ሁላችንም የሰው ልጆች የአንድ አባትና እናት ልጆች ነን፡፡ የአደምና ሀዋ፡፡ አንዲት ሰፊ አገርም አለን፡፡ እሷም መሬት/ምድር ትባላለች፡፡ ያለ ክፋት፣ ጥላቻና ምቀኝነት ስንሆን ለሁላችንም ትበቃለች፡፡ የሁሉንም አስተሳሰብና አመለካከት ባለቤቶች ሰፋ ባለ መልኩ ትይዛለች፡፡ ሆነብለን ካልተገፋፋን በስተቀር አዎን ምድር በቂያችን ናት፡፡ በነቢዩ ዘመን የታላቁ ነቢይ መናገሻ በሆነችው የመዲና ከተማ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖችና አይሁዶች ለዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ እንዴት ከተባለ – በሃይማኖት ማስገደድ ስለሌለ፣ ወደ ቀናው የእስልምና መንገድም ጥሪ የሚደረገው በጥበብና በመልካም ምክር ስለሆነ፣ በሃይማኖት ጉዳይ ሲከራከሩም እጅግ ባማረ ሥነምግባር ስለሆነ ነበር፡፡

ዛሬ ላይ ግን በዓለም ላይ የሚታየው የጊዜው የፈተና ዳመና፣ የአንዳንድ ሙስሊሞች ጥፋት፣ የዓለም ፖለቲካ ተንኮልና የሚዲያ ግነት ተደምሮበት ሙስሊሙ በዲኑም ሆነ በዱንያው ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ በማህበራዊ ኑሮም ከዚህም ከዚያም ለውግዘትና ለጥርጣሬ ዳርጎታል፤ መልካም ስሙንም አጠልሽቷል፣ ኢስላም ማለት ‹ሰላም› ነው የሚለውንም አባባል ጥያቄ ዉስጥ ከቶታል ፡፡ የሽብር.. ሥም ሲነሳ ሙስሊም አብሮ ይነሳል፡፡

እስልምና ገና ከጅማሮው የደምን ጉዳይ አክብዶታል፡፡ ከእስልምና ትላልቅ ዓላማዎች መካከል አንዱ የሰውን ልጅ ነፍስ መጠበቅ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡

አላህ ሱብሐኑ ወተዓላ የሰውን ልጅ ምድር ላይ ያስገኘው ለመልካም ዓላማ ነው፡፡ በዋናነትም አምልኮና የምድር ልማት፡፡ ይህን መልካም ዓላማውን ይፈጽሙ ዘንድ አላህ (ሱ.ወ.) የሰውን ልጆችን በምድር ላይ ምትክ እንደሚያደርግ ለመላኢኮች በገለፀ ጊዜ መላእክት ጠየቁ‹ ‹የሰው ልጅ በምድር ላይ በጥፋት ይሄዳል፣ ደምንም ያላግባብ ያፈሳል› በማለት፡፡ (የአል-በቀረህ ምዕራፍ ቁ-30) አላህም እነርሱ የማያውቁት ነገር እንዳለ ለመላእክቱ ነገራቸው፡፡ ብቻ ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር የሰው ልጅ ነፍስ የተከበረች መሆኗንና በግድያ ወንጀል ፍጡራን ሁሉ እንዴት እንደሚሸማቀቁ ነው፡፡

በኢስላም – ግድያ የወንጀሎች ሁሉ የበላይ ከሆነው በአላህ ከማጋራት የ(ሺርክ) ወንጀል ቀጥሎ ትልቁ ወንጀል ነው፡፡ ቁርኣን አንዲትን ነፍስ ያላግባብ መግደልን ሰዎችን በሙሉ እንደመግደል ነው ብሎታል፡፡ (አል-ማኢደህ፡ 32) ከዚህም ሌላ በርካታ ቦታዎች ላይ ከባባድ ማስጠንቀቂያዎችን አስተላልፎበታል፡፡

የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከእጅግ አደገኛና አጥፊ ወንጀሎች መካከል ሁለተኛ ላይ ቆጥረውታል፡፡ ነፍስን መግደል የሚያሳድረውን ትልቅ የሥነልቦና ተጽእኖ በሚገልፀው ሐዲሣቸው ደግሞ እንዲህ ይላሉ ‹አንድ ሙስሊም ሁሌም ሰላማዊና የተረጋጋ በሆነ ህይወት ውስጥ ነው የሚኖረው፤ አግባብ ባልሆነ መልኩ የሰውን ልጅ ደም እስካላፈሰሰ ድረስ፡፡› ብለዋል፡፡ በርግጥም የሰው ልጅ ነፍስ ትልቅ ዕዳ ናት፡፡ በሄደበት ሁሉ ገዳይን ትከተላለች፡፡

ሌላም እናክል – ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ‹በዕለተ ትንሳኤ በሰዎች መካከል ፍርድ የሚሰጠው በደም ጉዳይ ነው፡፡› ብለዋል፡፡ ይህም የጉዳዩን ክብደት የሚያሳይ ነው፡፡

እናም ከሰው ልጅ ደም አንፃር እስልምና ያለው አቋም በመጠኑ ይህን ይመስላል ለማለት ነው፡፡ እግረመንገዳችንንም እስልምና ከሰው ልጅ ደም አንፃር ያለውን እይታ በተመለከተ በተለይ ሙስሊም ባልሆኑት ዘንድ የተስፋፋውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር ከሙስሊሙ ብዙ ብዙ እንደሚጠበቅ ለማስታወስ ነው፡፡

#አሊፍ ራዲዮ