ጨረቃና መስቀል

0
4506

ጨረቃና መስቀል

‹የረመዳን ጨረቃ ከታየች …› ይላል ዜና አንባቢው …  ‹ምንድነው ጨረቃ ጨረቃ የሚሉት .?.›  ይላሉ ሙስሊም ያልሆኑቱ ደግሞ ግራ በመጋባት፡፡

 

በግምትም ይሁን ባለማወቅ እንደመስቀል ሁሉ ጨረቃን ከሙስሊሙ እምነት ጋር የሚያስተሳስሩ ወገኖች አሉ፡፡ በእስልምና ዉስጥ ጨረቃን በምልክትነት የመጠቀሙ ታሪክ መቼ እንደተጀመረ በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም በስፋት ጥቅም ላይ ዉሎ የታየው ግን በኦቶማን የኺላፋ ዘመን እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በጊዜው እስልምና በተለይ ወደምሥራቅ አውሮፓ እየተስፋፋ በመምጣቱና  የክርስቲያን አካባቢዎችን በማጥለቅለቁ ምክንያት መስጊድንና መሰል የእስልምና ተቋማትን ከሌሎች የእምነት ተቋማት ለመለየት ነበር ምልክቱ ያስፈለገው፡፡ ምናልባት ኦቶማኖች ጨረቃን የመረጡበት ምክንያት እምነታቸው ሰማያዊ መሠረት እንዳለው ለማመላከት ሊሆን ይችላል፡፡

ጨረቃ በመስጊድ ሚናራዎችና ቁባዎች ላይ እንደምልክት መደረጉና በተለያዩ ነገሮች ዉስጥም እስልምናን ለመግለጽ ጥቅም ላይ መዋሉ በነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ.) ሆነ በኸሊፋዎች ዘመን ያልነበረ ጉዳይ ስለመሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ነው፡፡ ከዚሁ በመነሳትም አንዳንዶች በመስጂድ ሚናራዎች ላይ የጨረቃን ምልክት ማስቀመጥ ቢድዓ/ በሃይማኖቱ ውስጡ የተደረገ አዲስ ፈጠራ ነው/ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከበጎ ልማዶችና ዉርሶች መካከል ቆጥረውታል፡፡ ጠቃሚነቱ ጎልቶ ከታየ፣ ፋይዳውም ካመዘነ መጠቀሙ ችግር የለውም ይላሉ፡፡

ጨረቃ እንደማንኛውም ፍጥረት ሁሉ የአላህ ፍጡር ናት፡፡ የጨረቃ መግባትም ሆነ መውጣት በሰው ልጅ ሕይወትም ሆነ ዕጣፈንታ ላይ ምንም ድርሻ የለውም፡፡ የሚጠቅምም ሆነ የሚጎዳ፣ የሚሠጥና የሚነሳ አላህ (ሱ.ወ.) ብቻ ነው፡፡ እኛ ሙስሊሞች የምናመልከው አላህን (ሱ.ወ.) ብቻ ነው፡፡ ከአላህ ዉጭ ወይም ከሱ ጋር አዳብለን ነቢይንም ሆነ ወሊይ፣ መልዓክ ሆነ ሌላ ሌላውን አናመልክም፡፡ ሙስሊሞች ጨረቃን የሚጠብቁት፣ በሷ ነው የሚያምኑት የሚል ካለ በርግጥ አስተሳሰቡ ስህተት ነው፡፡

የጨረቃ አቆጣጠር ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጆች የሚጠቀሙበት አቆጣጠር ነው፡፡ በጨረቃ መወለድ፣ ማደግና በመጨረሻም መክሰም ቀናትን፣ ጊዜያቶችን፣ የአንድን ወር መግቢያና መውጫ እናዉቃለን፣ ዘመናትን እንቆጥራለን፡፡ ጨረቃ  ከዚህም ባለፈ የተለያዩ ጥቅሞች አሏት፡፡ ለሌሊት ተጓዦችም የጎላ ፋይዳ አላት፡፡ ስለጨረቃ ምንነት ለሚጠይቁ አላህ (ሱ.ወ.) በቁርኣን ዉስጥ ምላሽ ሠጥቶበታል፡፡ ‹ስለ ለጋ ጨረቃዎች (መለዋወጥ) ይጠይቁሃል፡፡ እነርሱ ለሰዎች ጥቅም፣ ለሐጅም (ማወቂያ) ጊዜያቶች (ምልክቶች) ናቸው፡፡…› በላቸው፡፡› ይላል አላህ ሱ.ወ. (የአል በቀራ ዕራፍ ቁ- 189) ፡፡

ተከታዮቻቸው እየተጠቀሙባቸው ጨረቃም ሆነ መስቀልየእስልምናና የክርስትና ሃይማኖት ምልክት ሆነው ለዘመናት ዘልቀዋል፡፡ ስለ መስቀል ብዙ ማለት ባንችልም ስለ ጨረቃ የምንለው – ከአምልኮ ጋር የሚያይዛት ምንም ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ዛሬ በኢስላማዊው የጨረቃ አቆጣጠር ቀኑ  ሸዕባን …….. ነው፡፡ የሸዕባን ወር ጨረቃ 30 ከሞላ …….ቀን፤ ከጎደለ ደግሞ ነገ ………. ጾማችንን እንይዛለን ማለት ነው፡፡

አሊፎች መልካም ረመዳን ተመኘንላችሁ፡፡