ስለ አሊፍ ራዲዮ

በአላህ ስም እንጀምራለን
አሊፍ ራዲዮ  July 2013 ተመሰረተ ::

የአሊፍ ራዲዮ ዝግጅት ክፍል ራዕይ

      ረቂቅ

አሊፍ ራዲዮ ከትክክለኛው ምንጭ የተቀዳውንና ሚዛናዊውን እስልምና ግልፅ፣ ቀላልና ውብ በሆነ አቀራረብ በሀገር ወስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ለሚገኙ ኢትዮጲያውያን ሙስሊሞች በተሻለ ጥራትና ይዘት ይተላለፍ ዘንድ መድረኩን ለማመቻቸት ተነሳሽነቱ ባላቸው አካላት የተቋቋመ ራዲዮ ነው፡፡ በርግጥ መልእክቱን ለመቋደስ ለፈለገ ማንኛውም አካል መድረኩ ክፍት ነው፡፡

 

የአለማችን ታላላቅ የኢስላም ምሁራን የሚጋሩት እውነታ ቢኖር ሙስሊሙ ህብረተሰብ በሚኖርበት በየትኛውም የአለም ክፍል በየዘመናቱ የሚገጥሙት የማንነት ቀውሶች እንዲሁም የእምነት መሰናክሎች በአይነትም ሆነ በብዛት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መሆኑን ነው፡፡ይህንን በእምነታችን ላይ የተጋረጠ አደጋ መጋፈጥ ለነገ የማይባል የሁላችንም ተግባር ነው፡፡

 

እኛም ይህንን መነሻ በማድረግ በተለይ በኢትዮጲያውያን ሙስሊሞች ላይ ለዘመናት የሚታዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ችግሮቻቸውን በዘለቄታዊ ሁኔታ ለመቅረፍ የሚቻልበትን አግባብ በመመርመርና ከአለማችን ተጨባጭ ጋር ተግባቦትን በመፍጠር በቀጥተኛው መንገድ መጓዝ የሚችል ማንነትን እንዲያዳብር የበኩላችንን ጥረት ለማድረግ ወደናል፡፡

 

  ተልእኮ

ከላይ የተጠቀሰውን ራዕችንን እውን ለማድረግ በረጅምና አጭር ጊዜ የተቀመጡ የፖሊሲ አውታሮች ቢኖሩም ከሁሉም በፊት ከዚህ ቀውስ ነፃ ለመውጣት ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራበት የሚገባውና በትኩረት ሊጤን የግድ የሆነው ጉዳይ ግን የአመለካከት (የአስተሳሰብ) መስተካከል  ነው፡፡

ኢስላም የእውቀትን ምንነት በማብራራትም ሆነ እንዴት ሊቀሰም እንደሚችል በሚሰጠው ትንታኔ ከዘመናዊው የትምህርት ስርአት ጋር መሰረታዊ የፅንሰ-ሐሳብ ልዩነት አለው፡፡

እንደ ኢስላም እይታ የመሰረታዊ እውቀቶች መነሻና የመጀመርያ ምንጮች መለኮታዊ የሆኑት የአላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ቃል የሆነው ቁርአንና የመልእክተኛው ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ፈለግ የሆነው ሱና ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በነዚህ ምንጮች የሰፈሩትን መልእክቶች ማስተንተንና ሚዛናዊ አመክንዮን በመጠቀም ወደተግባር መቀየር የጠቢብነት መገለጫ ከመሆንም አልፎ ፍጥረተ-ዓለሙን የምንመለከትበት ኢስላማዊ እይታን በማጎልበት እውነትንና እውቀትን አጣምሮ ማራመድ የሚያስችል ፅንሰ-ሐሳብ ባለቤት ያደርጋል፡፡ ዘመናዊው የትምህርት አሰጣጥ ሂደት በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው አዕምሮን ማናገር ላይ በመሆኑ ለአለም የሚኖረው እይታ መሰረታዊ ልዩነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡

ይህንን ችግር በጥልቀት ለመረዳት እንደ ኢስላማዊ የስነ- መለኮት ጥናት እና ፊቂህ ያሉ የእውቀት ዘርፎችን ታሪካዊና ምሁራዊ መሰረታቸውን መገምገም ይጠቅመናል፡፡ እነዚህ የትምህርት ዘርፎች በፍልስፍናው፣ በስነ- አመክንዮው፣ በሰነድ አሰባሰብ ስርአትና በመሳሰሉት ያበረከቱት አስተዋፅኦ የአእምሮ ስራ ብቻ እንዳልሆነ ህያው ምስክር ናቸው፡፡

 

ሌላውና የዘመናችን ትልቁ ራስ ምታት ከእውነታ የራቁና ምንጫቸው የማይታወቁ በርካታ መረጃዎች ተደራሲያቸውን ከፍተኛ የንቃት ደረጃ ላይ እንደደረሰ እንዲያምን ስለሚያስገድዱት ሁሉም ያወቀ እንዲመስለው ይሆናል፡፡ ኢስላምን ከዚህ የሚለየው በጠነከረ ሰንሰለታማ ተዋረድ በተላለፈና መልካምነታቸው በተመሰከረላቸው ግለሰቦች በተዘገቡ ተአማኒ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ እውቀትን በማስጨበጡ ነው፡፡ አንድ ሰው እውቀትን ሲቀስም ከማን፣ እንዴትና በምን ሁኔታ መቅሰም እንዳለበት ከሚወስደው ጥንቃቄ ባሻገር በሚያገኘው እውቀት ራስን ለማስተካከልና ወደ ተግባር በመቀየር ሊገኝ የሚችለውን ጥቅምና መገጠም(ተውፊቅ) ለመቋደስ ልዩ ጉጉትና ተነሳሽነት ይኖረዋል፡፡

 

የአሊፍ ራዲዮ የትኩረት አቅጣጫ የተለያየ የአመለካከት ዳራ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መሰረት በማድረግ የተቃኘ ሲሆን በዚህም ከወገንተኝነት ነፃ የሆነና አንድነትን የሚያጠናክር ፕግራም በማዘጋጀትና በማሰራጨት ይገለፃል፡፡ አሊፍ ራዲዮ የሚያቀርባቸው ፕሮግሞች በሙሉ ኪናዊ ይዘታቸውን የጠበቁ፣ እንደ ርዕሰ ጉዳዩ አይነትና ስፋት የበቁ ባለሙያዎች የሚሳተፉበትና በእውቀትና በመረጃ የበለፀጉ ሁሉን አቀፍ እንዲሆኑ መትጋት የዝግጅት ክፍሉ አብይ መርህ ነው፡፡

 

አሊፍ ራዲዮ የዕውቀት መድረክ