እንተዋወስ

0 4486
Jumairah Mosque with half moon

ጨረቃና መስቀል

‹የረመዳን ጨረቃ ከታየች …› ይላል ዜና አንባቢው …  ‹ምንድነው ጨረቃ ጨረቃ የሚሉት .?.›  ይላሉ ሙስሊም ያልሆኑቱ ደግሞ ግራ በመጋባት፡፡

 

በግምትም ይሁን ባለማወቅ እንደመስቀል ሁሉ ጨረቃን ከሙስሊሙ እምነት ጋር የሚያስተሳስሩ ወገኖች አሉ፡፡ በእስልምና ዉስጥ ጨረቃን በምልክትነት የመጠቀሙ ታሪክ መቼ እንደተጀመረ በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም በስፋት ጥቅም ላይ ዉሎ የታየው ግን በኦቶማን የኺላፋ ዘመን እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በጊዜው እስልምና በተለይ ወደምሥራቅ አውሮፓ እየተስፋፋ በመምጣቱና  የክርስቲያን አካባቢዎችን በማጥለቅለቁ ምክንያት መስጊድንና መሰል የእስልምና ተቋማትን ከሌሎች የእምነት ተቋማት ለመለየት ነበር ምልክቱ ያስፈለገው፡፡ ምናልባት ኦቶማኖች ጨረቃን የመረጡበት ምክንያት እምነታቸው ሰማያዊ መሠረት እንዳለው ለማመላከት ሊሆን ይችላል፡፡

ጨረቃ በመስጊድ ሚናራዎችና ቁባዎች ላይ እንደምልክት መደረጉና በተለያዩ ነገሮች ዉስጥም እስልምናን ለመግለጽ ጥቅም ላይ መዋሉ በነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ.) ሆነ በኸሊፋዎች ዘመን ያልነበረ ጉዳይ ስለመሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ነው፡፡ ከዚሁ በመነሳትም አንዳንዶች በመስጂድ ሚናራዎች ላይ የጨረቃን ምልክት ማስቀመጥ ቢድዓ/ በሃይማኖቱ ውስጡ የተደረገ አዲስ ፈጠራ ነው/ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከበጎ ልማዶችና ዉርሶች መካከል ቆጥረውታል፡፡ ጠቃሚነቱ ጎልቶ ከታየ፣ ፋይዳውም ካመዘነ መጠቀሙ ችግር የለውም ይላሉ፡፡

ጨረቃ እንደማንኛውም ፍጥረት ሁሉ የአላህ ፍጡር ናት፡፡ የጨረቃ መግባትም ሆነ መውጣት በሰው ልጅ ሕይወትም ሆነ ዕጣፈንታ ላይ ምንም ድርሻ የለውም፡፡ የሚጠቅምም ሆነ የሚጎዳ፣ የሚሠጥና የሚነሳ አላህ (ሱ.ወ.) ብቻ ነው፡፡ እኛ ሙስሊሞች የምናመልከው አላህን (ሱ.ወ.) ብቻ ነው፡፡ ከአላህ ዉጭ ወይም ከሱ ጋር አዳብለን ነቢይንም ሆነ ወሊይ፣ መልዓክ ሆነ ሌላ ሌላውን አናመልክም፡፡ ሙስሊሞች ጨረቃን የሚጠብቁት፣ በሷ ነው የሚያምኑት የሚል ካለ በርግጥ አስተሳሰቡ ስህተት ነው፡፡

የጨረቃ አቆጣጠር ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጆች የሚጠቀሙበት አቆጣጠር ነው፡፡ በጨረቃ መወለድ፣ ማደግና በመጨረሻም መክሰም ቀናትን፣ ጊዜያቶችን፣ የአንድን ወር መግቢያና መውጫ እናዉቃለን፣ ዘመናትን እንቆጥራለን፡፡ ጨረቃ  ከዚህም ባለፈ የተለያዩ ጥቅሞች አሏት፡፡ ለሌሊት ተጓዦችም የጎላ ፋይዳ አላት፡፡ ስለጨረቃ ምንነት ለሚጠይቁ አላህ (ሱ.ወ.) በቁርኣን ዉስጥ ምላሽ ሠጥቶበታል፡፡ ‹ስለ ለጋ ጨረቃዎች (መለዋወጥ) ይጠይቁሃል፡፡ እነርሱ ለሰዎች ጥቅም፣ ለሐጅም (ማወቂያ) ጊዜያቶች (ምልክቶች) ናቸው፡፡…› በላቸው፡፡› ይላል አላህ ሱ.ወ. (የአል በቀራ ዕራፍ ቁ- 189) ፡፡

ተከታዮቻቸው እየተጠቀሙባቸው ጨረቃም ሆነ መስቀልየእስልምናና የክርስትና ሃይማኖት ምልክት ሆነው ለዘመናት ዘልቀዋል፡፡ ስለ መስቀል ብዙ ማለት ባንችልም ስለ ጨረቃ የምንለው – ከአምልኮ ጋር የሚያይዛት ምንም ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ዛሬ በኢስላማዊው የጨረቃ አቆጣጠር ቀኑ  ሸዕባን …….. ነው፡፡ የሸዕባን ወር ጨረቃ 30 ከሞላ …….ቀን፤ ከጎደለ ደግሞ ነገ ………. ጾማችንን እንይዛለን ማለት ነው፡፡

አሊፎች መልካም ረመዳን ተመኘንላችሁ፡፡

 

0 4590

በረመዳን ተውባ ለምን?

ሙስሊም በመሰረቱ ሁሌም ተውባ ማድረግ አለበት፡፡ በየቀኑ፣ በየደቂቃና ሰከንዱ ወደ ጌታው መመለስ አለበት፡፡ ተውባ ማለት  አጥፍቻለሁ ዳግመኛ አይለምደኝም በማለት ወደ አላህ መመለስ ነው፡፡ ተውባ ጥፋትን ማመን፣ በሳለፉት ጥፋት መፀፀትና ዳግም ላለማጥፋት ቁርጠኛ ሀሳብ ማኖር ነው፡፡ የተውባ ዓላማው ለመሻሻል ነው፡፡ ከወንጀል ወደ ፅድቅ፣ ከጥፋት ወደ ልማት መምጣት ነው፡፡

ተውባ በእስልምናችን ግዴታ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሆኖ የማያጠፋ ማንም የለምና ሁሉ ተውባ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ተውባ የአላህ ነቢያትና የደጋግ ሰዎች መንገድ ጭምር ነው፡፡ ብዙዎች ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ስህተታቸው ወደ አላህ ተመልሰዋል፣ አላህም ተውባቸውን ተቀብሏቸዋል፡፡ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) በመመለስ ረገድ አባታችን አደም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ የተከለከሉትን ዛፍ በበሉ ‹ጌታችን ሆይ ነፍሳችንን በድለናልና አንተ ባትምረንና ባታዝንልን ከከሳሪዎች እንሆናለን› በመላት ነበር ወደ አላህ (ሱ.ወ.) የተመለሱት፡፡  የኛው አርዓያና ሞዴል የሆኑት ታላቁ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) ‹እኔ በቀን ዉስጥ ከሰባ ጊዜ በላይ ከአላህ ምህረትን እለምናለሁ፣ ወደርሱም እመለሳለሁ፡፡› ይሉ ነበር፡፡

በየቀኑ፣ በየደቂቃና ሰከንዱ ወደ አላህ መመለስ የቻለ ሰው መልካም፡፡ አላህ ይጨምርለት፡፡ ተዘናግቶ የከረመውን ደግሞ አላህ መዘናጋቱን ያንሳለት፡፡ አላህ ሁላችንንም ይመልሰን፡፡ ለእውነተኛ ተውበትም ይወፍቀን፡፡

ረመዳን ሲደርስ ብዙ ሰዎች ወደ አላህ መንገድ ይመለሳሉ፣  ወደ መስጊድ ፊታቸውን ይመልሳሉ፣ ወደፈጠራቸው አምላክ  ልቦናቸውን ያዞራሉ፡፡ ረሐረመቱን ከጅለው ነው የሚመጡት፣ እሱ ያከበረውን ወር አክብረው ነው የሚመለሱት፡፡ ስለሆነም ለምን መጣችሁ ተብለው መወቀስ የለባቸውም፣ መስጊድ ቢመጡም ሆነ መልካም ነገር ላይ ቢሳተፉ የጎሪጥ መታየት የለባቸውም፡፡

ረመዳን የተውባ ወር ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ወር ዉስጥ ተውባችንን ይበልጥ ማደስ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ወሩ የአላህ (ሱ.ወ.) እዝነት በስፋት የሚወርድበት ወር ነውና፡፡ ፍጥረቱ ሆኖ ከእዝነቱ የተብቃቃ ማን አለና፡፡ በረመዳን ይበልጥ ወደ አላህ እንመለሳለን፡፡ የደረቀው ቀልባችንን እንዲርስ እንፈልጋለን፣  የረሕመቱ ወር በረከት ለኛም እንዲደርሰን እንከጅላለን፣ ለአላህ ባሮች የተከፈተው ሰፊ ችሮታው ለኛም ይደርሰን እንመኛለን፣ ለጥፋታችን ምህረቱን እንጠይቃለን፣ አላህ በዲኑ ላይ ያፀናን ዘንድ እንማፀነዋለን፡፡

በረመዳንም ሆነ በሌላ ጊዜ ወደ አላህ እንመለሳለን፣ አላህ (ሱ.ወ.) በከፈተልን የተውባ በር እንገባለን፣ የተሠጠንንም ዕድል እንጠቀምበታለን፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ያጣናቸውን ችሮታዎች ለማግኘት እንጓጋለን፣ ከአምላካችን ጋር እንታረቃለን፣ ፅናቱን ይለግሰን ዘንድ እንለምነዋለን፡፡ በወሩ ዉስጥ መልካሙን ነገር እንዳገራልን ከወሩ ዉጭም እንዲያገራልን እንማፀነዋለን፡፡

አላህ (ሱ.ወ.) ባሪያው በየትኛውም ጊዜ ስህተቱን አምኖ፣ በጥፋቱ ተፀፅቶ ወደርሱ በመጣ ጊዜ እስከዛሬ የት ነበርክ ብሎ አያባርርምና፣ እሱ ከወላጅ እናትም በላይ አዛኝ አምላክ ነውና ያለፍራቻና ይሉኝታ ወደ አላህ እንመለሳለን፡፡ ከረመዳን በፊት በተለያዩ ወንጀሎች ቆስለናልና፣ በሐራም ነገሮችም ብዙ ተበክለናልና ከቁስላችን መፈወስ እንፈልጋለን፣ ከህመማችን መዳን እንሻለን፡፡ ለዚህም የርሱ ችሮታ ያስፈልገናልና ወደርሱ እንመለሳለን፡፡

አላህ መመለሳችንን ይቀበለን፡፡ በተውበታችን ላይ ያፅናን፡፡ አሚን

 

 

0 6237

ሸዕባን ሆይ እንኳን ደህና መጣህልን!

ጊዜው ይሮጣል… ዕድሜያችንም እንደዚያው ይሮጣል፡፡ ዐጃኢብ በሚያሠኝ መልኩ በርካታ ቀናት አለፉ፣ ወራትም በተከታታይ ነጎዱ፡፡ እነሆ የተባረከው  የረመዳን ወር ቀናት ፊትለፊታችን ተደቅነዋል፣ ምርጡ ወርም ሽታው አዉዶናል፡፡

ሸዕባን የታላቁ ረመዳን ወር መግቢያ ላይ ያለ ወር ነው፡፡ የሰው ልጅ የዓመት ሥራዎች የሚገመገሙበት እና ለአላህ (ሱ.ወ.) የሚቀርቡበት ወርም ነው፡፡ ታላቁ ዓሊም ኢብኑ አልቀይም አልጀዉዚ (አላህ ይዘንላቸው) እንዲህ ብለዋል – ‹የአላህ ባሮች ሥራዎች አላህ ዘንድ የሚቀርቡት በሸዕባን ወር ዉስጥ ነው፡፡ ሰኞ እና ሀሙስ የሳምንት ሥራዎች አላህ ዘንድ የሚቀርቡት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የየዕለት ሥራዎች ደግሞ በቀናት መጨረሻዎች ላይ አላህ ዘንድ ይቀርባሉ፡፡ የየለሌሊት ሥራዎች ደግሞ ከንጋት በፊት ይቀርባሉ፡፡ የሰው ልጅ የምድር ላይ ዕድሜ ያበቃ እንደሆነ የህይወት ዘመን ሥራ በሙሉ ወደ ላይ ይወጣል፤ በመጨረሻም የአንድ ሰው የሥራ ፋይልም ይዘጋል፡፡›

ስለሆነም ሸዕባን የሰው ልጅ የዓመት ሥራ በጀት የሚጠናቀቅበት ወር ይመስላል፡፡ ዓመቱን በመልካም ሁኔታ ያሳለፈ ደስ ይበለው፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከወራት ሁሉ በተለየ መልኩ የሸዕባንን ወር በብዛት ይፆሙ ነበር፡፡ ከእናታችን ዓኢሻ (ረ.ዐ.) እንደተወራው ‹የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) የሸዕባንን ወር አብዛኛውን ይፆሙ ነበር፡፡› ብለዋል፡፡

በሌላም ሐዲሥ ‹ሙሉውን አሊያም ጥቂቱ ብቻ ሲቀር ይፆሙ ነበር፡፡› ብለዋል፡፡

ስለሆነም የሸዕባንን ወር መፆም የሚወደድ ነው፡፡ ምክንያቱም የነብያችን ፈለግ ነውና፡፡ ሆኖምግን ከረመዳን አጋማሽ በኋላ እና ሸዕባን ሊያልቅ አካባቢ ለረመዳን አንድ እና ሁለት ቀን ሲቀረው እንዳንፆም ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ከልክለዋል፡፡ በፊት የሱና ፆሞችን ማለትም ሰኞ እና ሐሙስን ይፆም የነበረ ሰው ሲቀር፡፡ ለምሳሌ የመጨረሻው የሸዕባን ቀን ሰኞ አሊያም ሐሙስ ላይ ቢዉል አንድ ሰው ቢፆም ችግር የለውም፡፡ የፆመው በምክንያት ነውና፡፡

ዑለማኦች እንደሚሉት ከረመዳን አንድ እና ሁለት ቀን አስቀድሞ መፆም የተከለከለበት ምክንያት ረመዳንን እና ሸዕባንን ግልጽ ባለ መልኩ ለመለየት እንዲቻል ነው፡፡

የሸዕባን ወር አጋማሽ ፆም

የሸዕባንን ወር አጋማሽ ስለመፆም የተነገሩ ዘገባዎች አሉ፡፡  እነኚህ ሐዲሦች ደካማ መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ በዚህ ዙሪያ የተነገረ አንድም ጠንካራ ሐዲሥ የለም፡፡ እንደማንኛውም ወር ሁሉ ከየወሩ ሦስት አጋማሽ ቀናትን ማለትም 13ኛ፣ 14ኛ እና 15ኛውን ቀን መፆም ይቻላል፡፡ እነኚህ ቀናት አያም አልቢድ ይባላሉ፡፡ እነርሱም ጨረቃ ደምቃ የምትታይባቸው ቀናት ናቸው፡፡ ስለሆነም ከደካማ  ሐዲሥ መረጃነት በሸዕባን ወር አጋማሽ ላይ የሚደረጉ ልዩ የአምልኮ ተግባራት ዉድቅ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

የሸዕባን ወር ፆም ትሩፋቶች

ከአቢ ሁረይራ (ረ.ዐ.) እንደተወራው ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በሆነ ወር ዉስጥ እንደሚፆሙት ሌላውን ወር ሲፆሙ አይቼ አላውቅም› አልኳቸው አለ፡፡ እርሣቸውም ‹የትኛው ወር ነው?› አሉት፡፡ ‹ሸዕባን› አልኳቸው አለ፡፡ እርሣቸውም (ሰ.ዐ.ወ.) ‹ሸዕባን በረጀብ እና በረመዳን መካከል ያለ ወር ነው፡፡ ሰዎች ከርሱ ይዘናጋሉ፡፡ የባሮች ሥራዎች ለአላህ የሚቀርቡበት ነው፡፡ ፆመኛ ሆኜ ሥራዬ አላህ ዘንድ እንዲቀርብ ስለምሻ ነው፡፡› አሉ፡፡

የሸዕባን ወር ፆም ከፊት ለፊቱ ለሚመጣው የረመዳን ወር ፆም ማለማመጃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ወደ አንድ ሥራ መግባት ሲፈልግ ደርቆ የከረመ ሰውነቱን እንደሚያሟሙቀው ሁሉ ወደ ረመዳን ከመግባቱ በፊት ሸዕባንን መፆሙ የረመዳን ወር ፆም እንዳይከብደው ያግዘዋል፣ አስቀድሞ ስለተለማመደ ድካም አያገኘውም ብርታት ይኖረዋል፣ በተነቃቃ መንፈስም ወሩን ይጾማል፡፡ ስለሆነም ለሚመጣው ረመዳን ካሁኑ ነፍስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፣ ከፆም በተጨማሪ በመልካም ሥራ ላይ ራስን ማለማመድ በጎ ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን  ነፍስ ማንኛውም ሥራ ይገራላት ዘንድ ከወዲሁ ማለማመድ ተገቢ ነው፡፡

ቀደምት ደጋግ ሰዎች ስለ ሸዕባን ወር ምን አሉ?

ኢብኑ ረጀብ እንዲህ ይላሉ – ‹ሸዕባን ወር የረመዳን ወር መግቢያ እንደመሆኑ መጠን በረመዳን ዉስጥ የተደነገገው ፆም ለሸዕባን  ተደነገገ፡፡ ቁርኣንን ማንበብም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ለረመዳን ዝግጅት ይረዳል፣ ነፍስ ሥልጠና ታገኛለች፡፡ የአላህ ትዕዛዛቶችም ይገሩላታል፡፡›

ሰለመህ ኢብኑ ኩሀይል ‹ሸዕባን ወር የቁርኣን ቃሪኦች ወር ነው› ይባል ነበር ብለዋል፡፡

ዐምር ኢብኑ ቀይስ ሸዕባን ወር የገባ እንደሆነ ሱቁን ይዘጋና ወደ ቁርኣን ፊቱን ያዞራል፡፡

አቡበክር አልበልኺ ደግሞ አንዲህ ይላል- የረጀብ ወር እንደ ዳመና አምጭ ነፋስ ነው፣ የሸዕባን ወር ደግሞ እንደ ዳመና ሲሆን ረመዳን ደግሞ አንደ ዝናብ ነው፡፡ በረጀብ ወር ዉስጥ ያልዘራ እና ያልተከለ በሸዕባን ዉስጥ ደግሞ የዘራዉን ያልተንከባከበ፣ በረመዳን ዉስጥ ምርቱን ማጨድ አያስብ፡፡›

አዎን ቀደምቶች በዚህ መልኩ ነቅተው ለረመዳን ይዘጋጁ ነበር፡፡ እኛስ እንዴት ተዘጋጅተን ይሆን?  ሰዎች በሚዘናጉበት ወቅት መንቃት ብልህነት ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ሸዕባን ላይ የመፆማቸው ሚስጢር ሰዎች ስለሚዘናጉ መሆኑን ተናግረዋል፣ ፆም ደግሞ ምርጥ የአምልኮ ተግባር ነው፡፡ እርሣቸው ወንጀል የሌለባቸው ከመሆናቸው ጋር እንዲህ ይላሉ፡፡

እነሆ በአላህ ችሮታና ፈቃድ ረመዳን በር ላይ ደርሰናል፡፡ ቀደምቶቹ ደጋጎች አላህ (ሱ.ወ.) ለረመዳን ያደርሣቸው ዘንድ ከብዙ ወራት በፊት አብዝተው ይማፀኑ ነበር፡፡ ረመዳን ታላቅ ወር ነውና፡፡ ወሩ ደርሰው ለመፆም ያልታደሉም ብዙ ናቸው፡፡ ለሸዕባን ወር ስላደረሰን አላህን (ሱ.ወ.) አብዝተን እናመስግን፡፡ ለረመዳን ያደርሰን ዘንድም አምላካችንን እንማፀን፡፡

እንዲሁ እንደዋዛ ረጀብ አለፈ፣ ሸዕባን መጣ፣ ረመዳንም ሽታው አወደን፡፡ ስለሆነም ከወዲሁ ዝግጅት ያስፈልገናል፡፡ ሥራችን አላህ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ በንፁህ ልብ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) መመለስ ይኖርብናል፡፡

www.alifradio.com

 

 

 

0 5794

የረጀብ ወር ትርክቶች

አላህ (ሱ.ወ.) ሰውን ከሰው፣ ቦታን ከቦታ፣ ጊዜን ከጊዜ አበላልጧል፡፡ ይህንንም ያደረገበት የራሱ የሆነ ጥበብና ሚስጢር አለው፡፡ ጥበብና ሚስጢሩን ልናውቅም ላናውቅም እንችላለን፡፡ ከምናውቃቸው ጥበቦች መካከል የጊዜያትን ብልጫ ተገንዝበን በዕድሉ በመጠቀም በነርሱ ዉስጥ እንድንጠቀምና ይበልጥ ወደ አምላካችን እንድንቃረብበት ዘንድ ነው፡፡ ለምሳሌ ከወራት መካከል ረመዳን ትልቅ ትሩፋት ያለው ወር ነው፡፡ ረመዳን ዉስጥ የሚሠሩ አምልኮዎች በሌሎቹ ወራት ዉስጥ ከሚሠሩት በተለየ ሁኔታ ምንዳቸው ተነባብሮ ይከፈለናል፡፡ በወሩ ዉስጥ ከሺህ ቀናት የምትበልጥ አንዲት ሌሊት አለች፤ እሷን መጠቀም መቻል ትልቅ ትርፍ ነው፡፡ ከሳምንቱ ቀናት ዉስጥም ጁሙዓ ትልቅ ቀን ነው፡፡ በዉስጧ ሳዐት አልኢጃባ የምትባል አላህ ዱዓእን የሚሰማበት ጊዜ አለች፡፡

በዓመት ዉስጥ አሥራ ሁለት ወራት አሉ፡፡ ከአሥራ ሁለቱ ወራት ዉስጥ አራቱ የተከበሩ ወራት ናቸው፡፡ ረጀብ፣ ዙል-ቂዕዳ፣ ዙል-ሒጃ እና ሙሐረም ይሠናሉ፡፡ በነኚህ  ወራት ዉስጥ የአላህን ድንጋጌዎች በመጣስ ራሣችንን እንዳንበድል አላህ (ሱ.ወ.) መክሮናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ይላል፡-

‹የወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ዉስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን አሥራ ሁለት ወር ነው፤ ከነርሱ ዉስጥ አራቱ የተከበሩ ናቸው፡፡ ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው፤ በነርሱ ዉስጥም ነፍሶቻችሁን አትበድሉ፡፡….›› (አት-ተውባ ፡ 36)

ቡኻሪና ሙስሊም ባስተላለፉት ዘገባ ነቢዩም ሰ.ዐ.ወ. በሐዲሣቸው ስለነኚህ ወራት ክቡርነት መስክረዋል፡፡ ይዘነው ያለው የረጀብ ወር አላህ (ሱ.ወ.) ክብር ከሠጣቸው አራቱ ወራቶች መካከል አንዱ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ከዚህ ዉጭ ስለ ረጀብ ወር ብልጫና ልዩነት በቁርኣንም ሆነ በሶሒሕ ሐዲሥ የተላለፈ ልዩ መልዕክት የለም፡፡

ሆኖምግን የረጀብ ወር ሌሎች ተጨማሪ ትሩፋቶች እንዳለው በሰፊው ሲነገር እንሰማለን፡፡ በዚሁ መነሻነትም ብዙዎች የረጀብን ወር ሙሉዉን አሊያም አብዛኛውን የወሩን ክፍል ሲፆሙ እንዲሁም ሌሎች ወደ አላህ ያቃርበናል ብለው የሚያስቡትን በርካታ ተግባራትን ለምሳሌ እርድ፣ ሶለዋት፣ ኢዕቲካፍ፣ ዑምራ፣ ሰደቃና የመሳሰሉትን በተለየ መልኩ ሲፈጽሙ እናያለን፡፡

እርግጥ ነው ስለ ረጀብ ወር ትሩፋት  ብዙ ዘገባዎች ተላልፈዋል፡፡ ሆኖምግን የሐዲሥ አጥኚ ሊቃዉንቶችና ዑለሞች እንዳሉት እነኚህን በረጀብ ወር ዙሪያ የተነገሩ መልዕክቶች  አንድም ደካማ አሊያም ዉድቅ ዘገባዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ተቀባይነት የላቸውም፡፡

ታላቁ ዓሊም አልሓፊዝ ኢብኑ ሐጀር ረሒመሁላህ እንደሚሉት – በረጀብ ወር ታላቅነት እና ከሱ የተወሰኑ ቀናትን በመፆሙ፣ አሊያም የተወሰኑ ሌሊቶችን በመቆሙ ዙሪ ለማስረጃ የሚሆን አንድም የተላለፈ ጠንካራ ሐዲሥ የለም፡፡ በርካታ ሐዲሦች የመጡ ቢሆንም ደካማና ዉድቅ ናቸው፡፡›[1] ብለዋል፡፡

በረጀብ ወር ዉስጥ ተከስተዋል ከሚባሉ ክስተቶች መካከል አንዱ ኢስራእ እና ሚዕራጅ (የአላህ መልዕክተኛ ሰ.ዐ.ወ. ወደ ሰማዩ ዓለም ያደረጉት ጉዞ) ነው፡፡ ይህ ቀን የሚውለው በረጀብ ሀያ ሰባተኛው ላይ ቀን ላይ እንደሆነ ብዙ አፈታሪኮችን እንሠማለን፡፡ በርግጥም የኢስራእ እና ሚዕራጅ ሌሊት በእስልምና ዉስጥ ትልቅ ቦታ የሚሠጠው ታሪካዊ ሌሊት ስለመሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖምግን ይህ ቀን የዋለው በተጠቀሰው ወርና ቀን ዉስጥ ስለመሆኑ ተኣማኒነት ባላቸው ሐዲሦች የተላለፈ ዘገባም የለም፡፡  ቀኑንም በፆም እና በዒባዳ አሳልፉ ተብሎ የተነገረ ልዩ መልዕክት የለም፡፡ ከኛ ወደ መልካም ነገር በመሽቀዳደም የሚታወቁት ቀደምት ኸሊፋዎችም ሆኑ ሶሐቦችና ታቢዒዮች አላደረጉትም፡፡

አልሓፊዝ ኢብኑ ሐጀር ፈትሑልባሪ በተሠኘው ኪታባቸው ዉስጥ ‹ኢስራእና ሚዕራጅ ስለተከናወነበት ወር ከአሥር በላይ አባባሎች ተገኝተዋል፣ ከነኚህም መካከል በረመዳን፣ በሸዋል፣ በረጀብ፣ በረቢዕ አልአወል እንዲሁም በረቢዕ አልኣኪር ያሉ አሉ፡፡[2] ብለዋል፡፡

ሸይኽ ኢብኑ ተይሚያ ረሒመሁላህ እንደሚሉት – ኢስራእ እና ሚዕራጅ በየትኛው ወር ዉስጥ እንደተደረገ የሚታወቅ መረጃ የለም፡፡›[3]

ስለ ፆም ጉዳይ ከተነሳ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) ከረመዳን ቀጥሎ በብዛት የሚፆሙት የሸዕባንን ወር እንደሆነ ሶሒሕ ዘገባዎች ተላልፈዋል፡፡ በቡኻሪና ሙስሊም በተላለፈው ዘገባ  እናታችንዓኢሻ  ረ.ዐ. እንዲህ ብለዋል –  የአላህ መልዕክተኛ የረመዳንን ወር እንጂ የትኛውንም ወር ሙሉውን ፆመው አያውቁም፡፡ አብዛኛውን ጊዜዉን የሚፆሙት ደግሞ የሸዕባንን ወር ነው፡፡›

ከኡሳማ ኢብኑ ዘይድ ረ.ዐ እንደተወራው ደግሞ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከሌሎች ወራቶች በበለጠ ሸዕባንን በብዛት ሲፆሙ አያለሁ አልኳቸው፡፡› አለ፡፡ እርሣቸውም  ‹(ሸዕባን) ሰዎች በረጀብ እና በረመዳን መካከል ሰዎች የሚዘናጉበት ወር ነው፡፡ ሥራዎች ወደ ዓለማቱ ጌታ ከፍ የሚደረጉበት ወርም ነው፡፡ ስለሆነም ፆመኛ ሆኜ ሥራዬ ከፍ እንዲል (እንዲቀርብ) እፈልጋለሁ፡፡ አሉኝ፡፡ ብለዋል፡፡ ሐዲሡን አቡ ዳዉድ፣ ነሳኢ እና ኢብኑ ኹዘይማ ዘግበውታል፡፡

ስለሆነም ከዚሁ በመነሳት ስለ ረጀብ ወር የተላለፉ ዘገባዎችም ሆነ ዘገባዎቹ መሠረት በማድረግ የሚፈፀሙ የተለያዩ የአምልኮ ተግባራት የእስልምና አስተምህሮ እንዳልሆኑ አውቀን መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ አንድን የአምልኮ ተግባር ለመፈፀም ስንነሳሳም ግልጽ የሆኑ የሸሪዓዉን አስተምህሮዎችና ተኣማኒነት ያላቸውን ዘገባዎች መሠረት ልናደርግ ይገባል፡፡ ካልሆነ በሃይማኖት ዉስጥ ዉድቅ እና የጥመት መንገድ በሆነው ቢድዓ ላይ ልንወድቅ እንችላለንና፡፡

[1]   تبيين العجب فيما ورد في فضل رجب ، لابن حجر

[2]    ابن حجر   فتح الباري ((7/242 243) الخلاف في وقت المعراج

[3] زاد المعاد لابن القيم ، 1/275

#በአሊፍ ራዲዮ #

0 829

ሶላታችን – ጀነታችን

 

ሰላት ከአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት አንዷና የሃይማኖቱም ምሰሶ ናት። ሶላት በአማኞች ላይ ግዴታ ናት፡፡ “ሰላት በምእመናን ላይ በወቅት የተወሰነች ግዴታ ናት።”  (አን-ኒሳእ፡103) ብሏል አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ።

የአላህ መልዕክተኛም (ሰ.ዐ.ወ.) ለሶላት ከፍተኛ አጽንኦት ሠጥተው አደራ ብለዋል፡፡ ይህችን ዓለም ሊሰናበቱ አካባቢ በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ጭምር  ‘ሰላት ሰላት ሰላት — (የሰላትን ነገር አደራ)’  ብለዋል።

ሶላት አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ጥቅሟ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ‘ ሐይየ ዐለ-ሰላህ ሐይየ ዐለል-ፈላህ/ ወደ ሰላት ኑ ወደ ስኬት ኑ !’ እያለ ሙአዚኑ በቀን ውስጥ አምስት ጊዜ የሚጣራው ያለምክንያት አይደለም። ሰላት ጥቅሟ ለኛው ስለሆነ ነው። በመስገዳችን እንጠቀማለን፣ በመተዋችን ደግሞ በዱኒያም ሆነ በአኺራም እንጎዳለን።

ፈጣሪያችን አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ከሱ የምንገናኝበት ሰላትን ይህል ትልቅ መድረክ ለኛ በመስጠቱ ሲበዛ እድለኞች  ያሰኘናል። እሱ ሰላትን ባያመላክተን ኖሮ እስቲ አምላካችንን እንዴት እናገኘው ነበር!።

ሰላት እጅግ ምርጧ የመንፈስ ምግብ ናት። የአላህን ውዴታ ታስገኛለች፣ እርካታና እርጋታን ታጎናፅፋለች፣ ለፊት ብርሃን፣ ለሰውነት ጤና፣ ለመንፈስ ማደሻ፣ ለሰውነት ማነቃቂያ ዓይነተኛ መድሃኒት ናት።

ሰላት በሐዘን ጊዜ አጽናኛችን ናት፡፡ ድካም ሲያጋጥመን ጉልበትና ብርታት፣ ብቸኝነት ሲወርሰን አጫዋቻች ናት። በሰላት ሀሣብና ጭንቀት ይለቃል፣ ድብርት ይርቃል፣ ልቦና ይሰፋል፣ ርዝቅ ይከፈታል፣ ፀባይ ያምራል፣  ምላስ ለመልካም ነገር ይገራል፣ ወንጀል ይረግፋል፣ ደረጃ ከፍ ይላል።

ሰላት ለክፉ ስሜት መጨቆኛ ልጓም፣ ለሸይጧን የጥመት ጥሪ ድል መንሻ መሣሪያ፣ ከመጥፎ ድርጊቶችና ወንጀሎች መጠበቂያ ጋሻ ናት። ሶላት ስንሰግድ ቅብዝብዝ ነፍሳችን ታርፋለች። ከርታታ ልባችንም አስተማማን መጠጊያ ታገኛለች።

ሐጃ ኖሮትና ጉዳይ ገጥሞት የዉስጡን መናገር ያሰበ ሰው ተጣድፎ ወደ ሰላት ይግባ፤ ብሦቱንም ይናገር፤ ጉዳዩንም ይዘርዝር። ፍራቻ የገባው፣ ጭንቀት የወጠረው፣ ሀዘን የወረሠው፣ ፈተና የከበደው፣ ችግር የተደራረበበት፣ ሸይጧን የተፈታተነው ሰው ከሰላት የበለጠ አማራጭ መፍትሄ የለውም። ነገሮች ከአቅም በላይ ሲሆኑብን በሁለት ረከዓ ሰላት ብቻ ተነስተን አምላካችንን ብንለምን ነገር ሁሉ ይገራልናል፤ ሸክማችን ይቃለላል ። ሀሣብ ሲጫነን፣ ዕዳ ሲወርሰን፣ ቀን ሲጨልምብን፣ ወዳጅ ሲለወጥብን፣ ኃይላችን ሲያልቅ፣ ጉልበታችን ሲዝል ተነስተን በሰላት እንቁም…. አዲስ ኃይልና ጉልበት እናገኛለን፣ ከሀሣብና ጭንቀት እናርፋለን። ታላቁ ነቢይ ሰላለሁዐለይህ ወሠለም አንድ ነገር ያሣሰባቸው እንደሆን ፈጥነው ለሰላት ይቆማሉ፡፡ يا بلال أرحنا بالصلاة ‘ቢላል ሆይ ! እስቲ በሰላት አሣርፈን ’ ይሉም ነበር።

ሰላት ወደ መጨረሻው ዓለም መጓዙ ለማይቀር የሰው ልጅ ትልቋ ስንቅ፣ የመቃብር ሕይወት ለሚጠብቀው በኒ አደም መልካም ወዳጅ፣ ጨለማ በሚወርሰው የቂያማ ቀን በሲራጥ ላይ አስተማማኝ ብርሃን፣ በአስጨናቂው ዕለተ ትንሳኤ ጥሩ ጥላ ከለላ፣ በምርመራ ጊዜ መልካም ሥራ ለጎደለው የሚዛን ማሟያ ናት ።

የሰው ልጅ የቂያም ቀን የመጀመሪያ ምርመራ የሚደረገው ስለ ሰላት ነው። እሷ ከተስተካከለች ነገሮች ሁሉ ይስተካከላሉ፡፡ ከተበላሸችም ነገሮች ሁሉ ይበላሻሉ።

ሰላት የሌለዉ ሰው ዲን የለውም። ሰላት የሌለው አሊያም በቸልተኝነት የዘነጋ ሰው እርካታም ሆነ እርጋታ የለውም፡፡ በሰላት ሙስሊምና ካፊር ይለይበታል። ለአላህ ታዛዠ እና አመፀኛ የሆነው ሰው ይታወቅበታል።

ሰጋጅ ሰው ግን ዛሬ እውነተኛ ደስታና ውስጣዊ ሰላም አለዉ፡፡ ነገ ደግሞ

 

“ እነዚያ ሰላቶቻቸዉን ወቅቷን ጠብቀው የሚሰግዱ፣ እነዚያ እነርሱ ወራሾች ናቸው፡፡ እነዚያ አልፊርደዉስን ( ላዕላይ ገነትን ) የሚወርሱት ከውስጧም ለዝንተ ዓለም ይኖራሉ።”  ( አል-ሙእሚኑን፡ 9-11)  ከሚባሉት ይሆናል።

የምንሰግደው  በዚህች ዓለም የተገኘንበትን ታላቁን ዓላማና ተልዕኮ ለመወጣት ነው። የሰው ልጅ በዚህች  ምድር  ላይ የመገኘቱ ሚስጢርና የኑሮው ትርጉም አላህን (ሱ.ወ.) ማምለክ፣ ባርነትን ለሱ መግለጽ፣ መገዛትንና መታዘዝን ለሱ ማሳየት ነው። ምርጡ መገዛት (አምልኮ) ደግሞ ሰላት ነው። በግዴታ ይሁን በሱና ሰላቶች በአላህ (ሱ.ወ) ፊት መዋደቅና ግንባርን መሬት ማስነካት አላህ ያደለው ቢሆን እንጂ ማንም ተራ ሰው የሚያገኘው አይደለም። ስለሆነም ለአላህ የሚሰግድ ሰው የተከበረ ፍጡር ነው፡፡

እዉጭ ሆኖ ለሚያይ ሰው የመውደቅ መነሳት እንቅስቃሴ ይምሰል እንጅ እዉስጧ ለገባና ጥፍጥናዋንም ላጣጣመ ሰው ሰላት ጀነት ናት – የዱኒያ ላይ ጀነት። በሰላት ዉስጥ የመጠቀ የቀልብ ሰኪና፣ ልዩ የሆነ እርካታና እውነተኛ መረጋጋት አለና።

አዲሱን ቀኑን ከወፏና ከፀሐይዋ ቀድሞ አላህን እያወደሰ ከእንቅልፉ የተነሳና የሶላት ግዴታዉን በጀመዓ ለሰገደ ሰዉ ሙሉ ቀኑን የአላህ ጥበቃና ከለላ አለለት ።

በዱኒያ ላይ አንዲት ሰላት የምትበላ ጀነት አለች ዛሬ ከሷ ያልገባ ሰው የነገውንም የአላህ ድግስ ከዋናው ጀነት መግባቱን እንጃ! ።

0 679

ሲዋክ  – ከሱናነቱ  ባሻገር

ሰው ሠራሹ ቢላዋ ከትንሽ ጊዜ ግልጋሎት በኋላ ‹ዶልዱሜያለሁኝና ሞርዱኝ› ይላል። የፀጉር፣ የእንጨትም ሆነ የብረት መቁረጫ ማሽኖች ከቀናት ሥራ በኋላ ‹ደክሞኛልና ጥርሴን ቀይሩልኝ› ሲሉ ይጠይቃሉ። ከአላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ለሰው ልጅ የተበረከተው ጥርስ ግን ያለምንም መቀየርና መሞረድ ከዉልደት እስከ ህልፈት የሰውን ልጅ ያገለግላል። በርግጥ የሰው ልጅ እድሜው ማምሻ አካባቢ እንደማንኛውም የሰውነት ክፍሉ ሁሉ በአገልግሎት ብዛት ጥርሱ የሚዳከም፣ አሊያም የሚወልቅ ቢሆንም ከዚያ በፊት ግን ጥርስ በንፅህና የተያዘ እንደሆን  ትኩስ እና ቀዝቃዛ፤ ጠንካራ እና ለስላሣ ነገሮች እየተፈራረቁበት እየነጨና እየፈጨ በአማካይ ከስልሣ ላላነሱ ዓመታት ጊዜ ሰውን ይኻድማል። ዐጃኢብ ነው የአላህ ሥራ!!። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ አፈጣጠራችንን እናስተውል ዘንድ በሱረቱ ዛሪያት ቁጥር ላይ

     وفي أنفسكم أفلا تبصرون / በነፍሦቻችሁ ዉስጥ አታስተውሉምን ? /’› ሲል  ወደ ውስጣችን እንድንመለከት ያስታውሰናል።

በመሆኑም ይህ ለህልዉናችን ጠቃሚ የሆነው ጥርስ  ያለ እድሜው ጡረታ እንዳይወጣ፣ ያለ ጊዜው ግልጋሎት እንዳያቆም ጥንቃቄ ልናደርግለት ግድ ይላል። ይህም ሊጎዱት ከሚችሉ ነገሮች በመጠበቅ ሀላል ነገሮችን በመመገብ ሊሆን ይችላል። ለምን ቢባል አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ጥሩ ነገሮችን እንድንበላና መልካም ነሮችንም እንድንሠራ መክሮናል።

‹ እናንተ ያመናችሁ ሆይ ! ከለገስናችሁ ነገሮች መልካሞቹን ተመገቡ። ለአላህም አመስግኑ፤ እሱን ብቻ ታመልኩ እንደሆን።›  ( አልበቀራ ፡ 172 )

የአፋችን ጠረን ሁሌም ጥሩ ይሆን ዘንድ የጥርሣችንን ውበትና ጤናውን ለመጠበቅ ሸሪዓችን ሲዋክን በሱናነት መንገድ አድርጎልናል። ሲዋክን የዘነጋን እንደሆን የምንበላቸው ምግቦች በጥርሣችን መካከል ቀርተው ጥርሣችን የሚሊዮን ባክቴሪያዎች መራቢያ መሆኑ አይቀሬ ነው። ሲዋክ በተለይ በዉዱእና በሰላት ወቅት እጅግ አስፈላጊና የተወደደ ነው። ምናልባትም ይህ ሊሆን የቻለው አንድ ባሪያ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ፊት ሲቆም በጥሩ ጠረንና በንፁህ ሁኔታ ላይ ሆኖ መሆን እንዳለበት ለማሣሠብ ይመስላል ። ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም በዚሁ ዙሪያ ሲናገሩ  ‹በህዝቦቼ ላይ ማጥበቅ ባይሆንብኝ ኖሮ በያንዳንዱ የዉዱእ ወቅት ሲዋክ እንዲጠቀሙ ባዘዝኳቸው ነበር። › ብለዋል።

ይህ ሐዲሥ የሚያመለክተን ሲዋክ አስፈላጊነቱ ምን ያህል እንደሆነ ነው። ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ሲዋክ መጠቀምን እጅግ አብዝተው ይወዱ ነበር። በሞት አፋፍ ላይ ጭምር ሆነውም የእናታችን የእመት ዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ ወንድም የሆነው ዐብዱረሕማን ሲዋክ እየሠወከ ወዳሉበት በገባ ጊዜ በማመላከታቸው ዓኢሻ ሲዋኩን አርጥባ ሰዉካላቸዋለች። በሌላ ሐዲሣቸውም ‹መልአኩ ጅብሪል ሊዘይረኝ ሲመጣ ሲዋክ እንድጠቀም ይመክረኛል፡፡› ብለዋል ።

ከሲዋክ ሁሉ ምርጥ ነው የሚባለው ከአራክ እንጨት የሚሠራው ሲሆን ነቢዩም ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ይህንኑ እንጨት ይጠቀሙ ነበር። ሌላው ቀርቶ ከሰሐቦቻቸው ጋር መንገድ ሲሄዱ የሲዋክ ተክል ያዩ እንደሆን ሰሐቦቻቸው እንጨቱ ላይ ወጥተው እንዲቆርጡላቸው ያዙ ነበር።

ሲዋክ ከሱናነቱ ባሻገር ጥቅሙ ዛሬ የጥርስ ብሩሽ ብለን ከምንጠቀመው የፋብሪካ ዉጤት በላይ የላቀ ነው። ሲዋክ በተፈጥሮ ጥርስን ከባክቴሪያዎች ሊያፀዱ በሚችሉ ንጥረ ነገሮች የተሞላ ነው። ጥርስን ሊያበሰብሱ የሚችሉ ነገሮችንና ሌሎች እክሎችን ያስወግዳል። የድድ መቁሰልንና መድማትን ይከላከላል። የአፍ ጠረንን ትንፋሽን ጥሩ ያደርጋል። በጥርሣችን መካከል የሚፈጠሩ ባክቴሪያዎች  ለጥርሣችን ጎጂ የሆኑ ኢንዛይሞችን ሊያመነጩ ይችላሉ። እነዚህ እንዛይሞች የጥርስ ነጩ ክፍል የተሠራበትን ካልሲየም የተባለውን ንጥረ ነገር በመብላት ለጥርስ መቦርቦር ምክኒያት ይሆናሉ። በሌላ በኩል ደግሞ መጥፎ ሽታ ያለው ጋስ የሚያመነጩ ባክቴሪያዎች አሉ። ሲዋክ በተፈጥሮዉ እነኚህን ሁሉ ሊያፀዳና ሊያስወግድ የሚችል ንጥረ ነገር በውስጡ ስላለው በቀላሉ የሚገኝ ተፈጥሮአዊ ፀረ ጀርም (disinfectant) ነው ልንለው እንችላለን። በመሆኑም ሲዋክን አዘዉትረን ተጠቀምን ማለት አንድም ነቢያዊውን ሱና ተገበርን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የጥርሣችንን ጤና ጠበቅን ማለት መሆኑን አውቀን ይህን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመምታት ዓይነት የሆነው ጥቅም እንዳያመልጠን ልንሽቀዳደምበት ይገባል እንላለን ።

www.alifradio.com

 

 

0 4513

ሰባቱ ሷዶች

ቀልባችን ክው ብሎ በደረቀ ጊዜ – ሀሳባችንን የሚሰርቁና ቀልባችንን የሚያንሸራትቱ ሳይሆኑ ስለ ዘላለሙ አገራችንና ስለ አኺራችን የሚያስታውሱን ወንድሞችና እህቶች ብዙ ብዙዎች፤ አሁንም አሁንም እንደ አየር ሁሉ ያስፈልጉናል፡፡ ካልሆነ አናድግም እናልቃለን፣ አንቆምም እንወድቃለን፣ ሰው አንሆንም እንከስማለን፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን እኛው ራሳችን በተቻለን መጠን መልካም ነገራትን ልናበዛ ይገባል፡፡

‹ስለ ቫይታሚን ሷድ ሰምተን ይሆን!›  በሷድ ፊደል የሚጀምሩ መልካም ነገሮች መሆናቸው ነው፡፡

 1. صلاة ሶላት – በሱናውም፣ በሌሊቱም በግዴታውም ሶላት በርታ፤ ስገድ ሳትሰስትም   ዱዓእ አድርግ፡፡
 2.  صدقةሰደቃ – መፅውት፣ ከበሽታህ ትፈውሳለህ፣ የልብ እርካታ ታገኛለህ፣
 3. صبرሶብር – ዛሬ ላይ ትዕግስት የሚጠይቁ ነገሮች አቤት መብዛታቸው!
 4. صيامሲያም /ፆም – አምሳያ የለውም፣ አላህ ዘንድ እጅግ የተወደደ ነው፡፡
 5. صدقሲድቅ /እውነተኛ መሆን –
 6. صلة الرحم ሲለተ ረሒም /ዝምድናን መቀጠል- አላህ (ሱ.ወ.) ትልቅ አጽንኦት ሠጥቶታል፣ በዝምድናም አደራ ብሏል፡፡
 7. صحبة صالحةሷሒብ ሷሊሕ /መልካም ጓደኛ/ –

 

0 1037

ኢባዳን ማብዛት!”

ትናንትና ዛሬCommon Mistakes in Prayer namaz

ዲንን አጥብቆ የያዘ ማንኛውም ሙስሊም ኢባዳዎችን አጠናክሮ በመፈፀም፣ ሁሉንም ዚክሮች በቃላት ተመስጦ በማንበብ፣ ሌሎች ወደ አላህ የሚያቃርቡ አምልኳዊ ተግባራትን በመከወን፣ በአላህ ዘንድ ትልቅ ደረጃ ካላቸው ደጋግ ባሮች ተርታ መሰለፍ እና አኼራዊ ስኬትን መቀዳጀት ይፈልጋሉ፡፡

በተለይ ደግሞ፣ ቀጥለን ለናሙና ያህል የምንጠቅሳቸውን አይነት ታሪኮች በሚሰሙበት ወይም በሚያነቡበት ጊዜ ፍላጎታቸው ይጨምራል፡-

 • ሱሀይል ቢን አምር (ረ.ዐ) (ሶላት፣ጾምና ሶደቃ የሚያበዛ ሰው ነበር) በአላህ መንገድ ለመታገል ወደ ሻም በተጓዙበት አንድ አጋጣሚ ቀን ጾመው ሌሊት መልካቸው እስኪቀያየር ድረስ ሲሰግዱ ማደራቸው ይነገራል፡፡ ሱሃይል (ረ.ዐ) ቁርኣን ሲቀራ በሰሙ ቁጥር እምባ የሚቀድማቸው አይነት ሰው ነበሩ፡፡
 • አነስ ቢን ዒያድ ከታቢዒይ ታላላቅ ሊቃውንት መካከል አንዱ ስለነበሩት ሶፍዋን ቢንት ሰሊም ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፡- ይኸውና ቂያማ ሊቆም ነው ቢባሉ አሁን እየሰሩ ካሉት ኢባዳ የሚጨምሩት የላቸውም፡፡
 • አህመድ ቢን ሰለማህ አን-ኒሳቡሪይ ስለ ሁናድ ቢን አስ-ሱሪይ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፡- ለቅሶ ያበዙ ነበር ቁርኣንን ሊቀሩልን ጊዜያቸውን ሰጡን፡፡ ዉዱእ አድርገው ወደ መስጂድ መጡና እስከ ቀትር ድረስ ሰገዱ፡፡ ከዚያም ተመልሰው ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ እንደገና ዉዱእ አድርገው መጡና ዙህር ሶላትን አሰገዱ፡፡ ከዚያም ቁርኣን ከፍተው እስከ መግሪብ ሶላት ድረስ ሲያነብቡ ቆዩ፡፡ አንድ ጎረቤታቸውን (አንተ) ዒባዳ ላይ እንዴት ያለ ታላቅ ትእግስት ነው ያላቸው ባክህ! አልኩት፡፡ ከዛሬ ሰባ አመት ጀምሮ የቀን ዒባዳቸው ይኸው ነው፣ የሌሊቱ ዓባዳቸውን ብታይ ደግሞ ከዚህም በላይ ትደነቃለህ አለኝ፡፡

ከነዚህም በላይ የሚያስደንቁ በርካታ ታሪኮችን ማቅረብ ቢቻልም ለማሳያ ያህል የተጠቀሱት በቂ ናቸው፡፡ አንድ ሙስሊም እነዚህንና ሌሎችንም መሰል ታሪኮችን በሚያነብብት ጊዜ ወይም በሚሰማበት ጊዜ ልቡ ይሰቀላል፡፡ ከነሱ አንዱ ስለመሆን ይመኛል፡፡ ነገር ግን ኑሮው አይፈቅድለትም ከተጨባጭ ህይወቱ ጋር ይላተማል፡፡ ጠዋት ከቤቱ የወጣ ሲዋከብ ውሎ ማታ የሚመለስ ለፍቶ አዳሪ ነው፡፡ ቤት ከገባ በኋላ ጎኑን ማሳረፍ ይኖርበታል፡፡ አለዚያ ለነገ የሚሆን ጉልበት አይኖረውም፡፡ ወይም ደግሞ ቤት ከገባ በኋላም በግሉ ወይም በቤተሰቦቹ ጉዳይ ተጠምዶ ያመሽ ይሆናል፡፡ በቃ በዚህ ሁኔታ ቀኑ ያልቃል፡፡ ከስራ በተረፈ ሰዓት ቢበዛ በማህበራዊ ጉዳዮች ቢሳተፍበት ወይም ጥቂት ገጾችን ቢያነብበት ነው፡፡ ከዚያ ወደ መኝታ ያመራል፡፡ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ተነስቶ እንደገና ወደ እለታዊ ስራ ይሄዳል፡፡ ዘወትር በዚህ ሁኔታ ውስጥ እየኖረ እንዴት አድርጎ ሰለፎች የሰሩትን ሁሉ ሊሰራ ይችላል፡፡

የዘመኑ ሰው ራሱን ከሰለፎች ጋር አወዳድሮ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንዳይፈጠርበት ወይም ታሪኮችን እንዳያስተባብልና ሌላ ጥፋት ውስጥ እንዳይነከር በጥቂቱም ትክክለኛ ማብራሪያዎች ያስፈልጉታልና ማብራሪያዎችን እነሆ፡-

 1. ዘመናችን ይለያል፡፡ ሰለፎች የቀናቸውን አብዛኛውን ጊዜ በስራ ለማሳለፍ በሚገደዱበት ሁኔታ ውስጥ አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ፡- አተባህ ቢን ጉላም ለእለት ጉርሱ የሚበቃውን ያህል ገቢ ካገኘ ይበቃው ነበር፡፡ በበሥራ ነዋሪዎች ዘንድ ኢባዳ በማብዛት ይታወቅ የነበረው ይኸው አትበሃ አጠቃላይ ካፒታሉ “1ብር” ብቻ ነበር፡፡ “ዋንኬ” ይገዛና ሰርቶ በሶስት ብር ይሸጠዋል፡፡ አንዱን ብር ለሰደቃ ሁለተኛውን ለእለት ጉርሱ መግዣ ያውለውና ሶስተኛውን (መነሻ ካፒታሉን) ያስቀምጠዋል፡፡

ዛሬ ያ ቀላል ህይወት ምድር ላይ የለም፡፡ በዚህ መልኩ ሰርቶ መኖር አይቻልም፡፡ አይቻልም ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም አይደለም፡፡ የዘመናችንን ልጓም ጨብጠን ክብርንና ነፃነታችንን ጠብቀን ለመኖር ሌትተቀን በርትተን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

 1. ጊዜያቸው በረካ ነበረው፡፡ በዘመናችን ጭራሽ የጠፋ የሚመስለው በረካ እነሱ ዘንድ የተትረፈረፈ ነበር፡፡ ለምን አዋቂው አላህ ነው! ምናልባት በቅንነታቸው ምክንያት ይሆናል፣ ምናልባት ለሃላል የነበራቸው ቀናኢነት…
 2. ኑሯቸው እንደኑሮዋችን ከባድ አልነበረም፡፡ እርግጥ ነው ቦታዎች ተቀራርበዋል የኑሮ ማቅለያ ዘዴዎች ተፈጥረዋል፡፡ ነገር ግን እጅግ ከለመድናቸው ከነዚህ የኑሮ ማቅለያ ዘዴዎች ውስጥ ድንገት አንዱ ሲጠፋብን ወይም ሲበላሽብን ምንያህል ነው የምንቸገረው ምንያህል ነው ከበርካታ ጉዳዮች የምንስተጓጎለው፡፡ መኪናው ቢበላሽ ሞባይሉ ቢጠፋ ወዘተ… እያልን ማሰብ እንችላልን፡፡
 3. ዛሬ ራስምታት የሆኑብንን በርካታ ነገሮች ሰለፎች አያውቋቸውም፡፡ የዛሬ ጭንቀቶቻችን ያን ጊዜ አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ- ዛሬ ልጆችን ከፈሳድ (ብልሹነት) ጠብቆ ማሳደግ ራሱን የቻለ ጭንቀት ነው፡፡ ብዙ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል፡፡ ሕይወታቸው ንፁህ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን እንደ አሸን የፈሉ የፈሳድ ሰበቦች ያኔ አንዳቸውም አልነበሩም፡፡
 • በሕይወት መቆየት ሌላ ፈተና ነው፡፡ ሐላል ሰርቶ፣ በቂ ገቢ አግኝቶ የራሱንና የቤተሰቦቹን ሕይወት ማቆየት በራሱ እጅግ ከብዷል፡፡ ሰለፎች ፍፁም በማያውቁት ሁኔታ የበርካታ ሀገር ዜጎች ጭንቀት ይኸው ነው፡፡ ራስንና ቤተሰብን አጥግቦ ከሌሎች ጥገኝነት ተላቆ ክቡር ሕይወትን መምራት ብርቅ ሆኗል፡፡
 • ሌላው ጭንቀት፡- በዘመናችን ለዲኑ ቀናኢ ሆኖ መገኘት በክፉ ያስጠረጥራል፡፡ አሸባሪ ያስብላል፡፡ በሙስሊም ሃገሮች የሚኖር ሙስሊም ዜጎች ለዲናቸው ያላቸው ፍቅር እንዳይታወቅባቸው በሚጨነቁበት ዘመን ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ለዲናቸው ያላቸው ክብረ ንጉሦቻቸው/መሪዎቻቸው ካወቁ ይከተሏቸዋል፡፡ ያስፈራሯቸዋል፡፡
 • ሌሎች በርካታ ጭንቀቶቻችንን መዘርዘር ይቻላል፡፡
 1. የኑሮ ሁኔታችን ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ዛሬ አላህ ካዘነላቸው ከጥቂቶች በስተቀር እያንዳንዱ ሰው ለወደፊት ሕይወቱ ለሥራ እና ለንብረቱ አብዝቶ በሚያስብበት ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ የልጆቹ የነገ ሕይወት ሥራቸውና ገንዘባቸውም እንዲሁ ያስጨንቀዋል፡፡ እነዚህን ሶስት ነገሮች ለራሱ እና ለልጆቹ ለማረጋገጥ ሲል ያለማቋረጥ ያስባል፡፡ ሌሎቹን ጉዳዮች ጊዜ እስኪያጣ ድረስ ያወጣል ያወርዳል፡፡
 2. በሙስሊም አገሮች የሚኖሩ ሙስሊሞች አምባገነን ንጉሶቻቸውን/መሪዎቻቸውን አስወግደው ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረትና ሰብኣዊ መብቶቻቸውን የሚያረጋግጡ ፍትሃዊ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ሙስሊም ባልሆኑ አገሮች የሚኖሩት ደግሞ እንደ ሙስሊም ማህበረሰብ ህልውናቸውን ለማረጋገጥ ጭቆናን አስወግደው፣ መገፋትን አስቀርተው የዜግነት መብቶቻቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረትና ትግል አብዛኛውን ጊዜያቸውን ይወስድባቸዋል፡፡ የዒባዳ ዓይነቶችን አብዝተው ለመፈፀም የሚችሉበት በቂ ጊዜ እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ ሰለፎችን የተመለከትን እንደሆነ በኸሊፋ ጥላ ስር ይኖሩ ስለነበር ከዚህ አንፃር የሚያደርጉት ትግል አልነበረም፡፡ የሚጠየቁት መስዋእትነት አልነበረም፡፡

ሚዛናዊነት በሙስሊም ሕይወት

አዘጋጅ .ሙሐመድ ሙሳ አሽሸሪፍ

ትርጉም አብዱልከሪም ታጁ

0 1666

 “ኢማሙ ሸዕቢ (ረ.ዐ) ስለሆነ ጉዳይ ፈትዋ እንዲሰጡ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ “አላውቅም” የሚል ነበር፡፡ ሕዝቡ “የዒራቅ ዋና ፈቂህ ሆነው አላውቅም ሲሉ አያፍሩም›› ? ሲላቸው ምላሻቸው “መላኢካዎች እንኳን ካሳወቀን ውጪ አናውቅም ሲሉ እኮ አላፈሩም፡፡ እኔ ለምን አፍራለሁ ?” የሚል ነበር ፡፡ “(አምካችን ሆይ!) አንተ ካስተማርከን ውጪ ሌላ ዕውቀት የለንም፤ (አልበቀራህ*32)
 ዑቅባህ ኢብኑ ሙስሊም አንጋፋ አሊም ከነበሩት ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) ጋር ለ 34 ወራት ቢቆዩም ሰዎች ወደሳቸው መጥተው በተለያዩ ኢስላማዊ ጉዳዮች ላያ ማብራሪያ እንዲሰጧቸው ሲጠይቁ የሚሰጧቸው ምላሽ “ይህንን አላውቅም” የሚል ነበር፡፡
 ሰዒድ ኢብኑ ሙሰይብም ፈትዋዎቻቸውን አስከትለው ሁሌም “ያ አላህ እኔም ሆነ ሌሎችን ከእኔ (ስህተቶች) ጠብቃቸው” ጠብቃቸው የሚል ዱዓ ያደርጉ ነበር ፡፡
 እንዲሁም ኢማሙ ሻፊዒ በሆነ ኢስላማዊ ጉዳይ ፈትዋ እንዲሰጡ ተጠይቀው ምንም ምላሽ ሳይሰጡ ዝም ብለው ቆዩ ፡፡ የተሰበሰበው ሕዝብ “ምላሽ አይሰጡንም እንዴ ?” ሲላቸው “ጥሩነቱ ያለው በዝምታዬ ወይም በምላሼ ውስጥ እንደሆነ እስከማውቅ ድረስ ነው” አሏቸው ፡፡
 ኢብኑ አቡ ለይላ አንድ መቶ ሃያ አንሳሮችን እንዳገኙ ይናገራሉ ፡፡ ታዲያ አንድ ጥያቄ ለአንደኛው አንሷርይ ሲቀርብ ያ አንሷሪይ ጥያቄውን ራሱ ሳይመልሰው ወደ ሌላ አንሷርይ ስለሚያስተላልፍ የተጠየቀው ጥያቄ መልስ ሳያገኝ ዞሮ ዞሮ ወደ መጀመሪያው ተጠያቂ ይመለስ ነበር ፡፡ ይህ የሚያሳየው ሁሉም የተሟላ እውቀት ላይኖረን ይችላል ከሚል ፍጹም መተናነስና በሚሰጡት ምላሽ ጠያቂውንም ሆነ ሕዝቡን ስህተት ላይ እንዳይጥሉ ካላቸው የአላህ ፍራቻ እንደሆነ እንረዳለን ፡፡
 አቡል ሑሴን አል-አዝዲ እንደተናገሩት በሶሓቦች ዘመን ዑመር ኢብኑ ኸጣብ (ረ.ዐ) በየትኛውም ጉዳይ ላይ ጥያቄ ሲጠየቁ ምላሽ ከመስጠታቸው አስቀድመው በድር ጦርነት ላይ ተሳትፈው የነበሩ ሶሓባዎችን ያማክሩ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
 ቃሲም ኢብኑ ሙሐመድ ፈትዋ እንዲሰጡ ተጠይቀው የተናገሩት የሚከተለው ነበር ፡፡ “ይህን ጉዳይ በተመለከተ ብዙ አላውቅም ፡፡ የፂምን ብዛትና ርዝመት እንዲሁም የከበቡኝን ሰዎች ብዛት አትመልከቱ ፡፡ በአላህ ይሁንብን በዚህ ጉዳይ እውቀት የለኝም እርግጠኛ ባልሆንኩበት ነገር ላይ ከመናገር ደግሞ አላህ ምላሴን ቆርጦ ይጣለው” የሚል ነበር ፡፡
 ሰልማን አል-ፋሪሲም በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለአቡ ደርዳእ ጽፈዋል፡- “ሌሎችን ሰዎች ለማከም ኃላፊነት እንደወሰድክ ሰምቻለሁ ፡፡ እውቀት እንዳላቸው እንደሚናገሩ፣ በተግባር ግን በእውቀትና ግንዛቤ ማነስ ህዝቡን በመጉዳት ላይ እንደተሰማሩት ሰዎች ከመሆን እራስህን ጠብቅ”
ከድንቃድንቅ ኢስላማዊ ወጎች የተወሰደ፡፡

0 1474

የአላህ ውዴታ . . .

አንድን ሰው አላህ ሲወደው የሰማያትም የምድርም ደጋጎች ይወዱታል። አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ያስተለለፉት ሐዲስ ይህን ያመለክታል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“አላህ አንድን ባሪያ በወደደው ጊዜ ጅብሪልን ይጠራና “እገሌን እወደዋለሁና ውደደው” ይለዋል። ጅብሪልም ይወደዋል። ከዚያም በሰማይ ውስጥ ጥሪ ያደርጋል። “አላህ እገሌን ወዶታልና ውደዱት” በማለት በሰማይ ውስጥ ጥሪ ያደርጋል። የሰማይ ነዋሪዎችም ይወዱታል። ከዚያም በምድር ላይ ሰውየው ተቀባይነት ይኖረዋል። አንድን ባሪያ ከጠላው ደግሞ ጅብሪልን ይጠራና፦ ይህንን ባሪያየን ጠልቸዋለሁና ጥላው።” ይለዋል። ጅብሪልም ይጠላዋል። ለሰማያት ነዋሪዎችም፦ “አላህ እገሌ የተባለውን ባሪያውን ጠልቶታልና ጥሉት።” ይላቸዋል። ይጠሉታል። ሰውየው በምድር ላይ ተቀባይነትን ያጣል።”

(ሙስሊም)