ማህበራዊና ሥነ ምግባር

ንግድ እና ነጋዴነት

በተለይ በሀገራችን ሙስሊም ማኅበረሰብ በንግድ ሥራ ይታወቃል፡፡ በዚህ ርእስ ሥር ስለ ንግድ እና የነጋዴው ባህሪ ምን መምሠል እንደሚኖርበት ጥቂት ነጥቦችን አብረን ለማየት እንሞክራለን-

በኢስላም ማንኛውም ሐላል የሆነ ሥራ ሁሉ ክቡር ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ለመኖር በሚያደርገው ግብግብ ሥራን ተስፋው አድርጎ ከመንቀሣቀሱ በተጨማሪ ወደ ጥሩና መልካም ነገሮችም መሸጋገሪያዬ፤ ወደ ጌታዬም መቃረቢያዬ ነው ብሎ ካሰበ ምንዳ በሚያስገኝ የአምልኮ ተግባር ይተረጎምለታል፡፡

መሥራት ሀሳብን ይሰበስባል፣ ሰውን ከድህነት ያጠራል፣ የሌሎችን እጅ ከማየት ያብቃቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠንካራ አማኝ በዒባዳው ላይ ይበልጥ ሊበረታ የሚችለው የሠራና የበላ እንደሆነ ነው፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ የሱን ሐቅ ከተወጣን በኋላ ራሣችንን እንድናግዝና ለሥጋችንም ጊዜ እንዲኖረን አነሣስቶናል፡፡  ከቁርኣን የሚከተሉትን አንቀፆች እንይ፡-

‹ ሰላትም በተጠናቀቀች ጊዜ በምድር ውስጥ ተበተኑ፤ የአላህንም ችሮታ ፈልጉ፡፡ › (አል-ጁሙዓ ፡10)

‹እርሱ ያ ምድርን የተገራች ያደረገላችሁ ነው፡፡ በጋራዎችና በተራራዎችም ሂዱ፡፡ ከሲሣዩም ብሉ፡፡›( አል-ሙልክ፡15)

የአላህን ችሮታ ከምንፈልግባቸዉ መንገዶች መካከል ንግድ አንደኛዉ ነው፡፡ ሐቀኛና እውነተኛ ነጋዴ የተከበረና አላህ በሚወደው ሥራ ላይ ነው፡፡ ማህበረሰቡን እየጠቀመ ፤ ሀገርና ወገኑንም በመርዳት ላይ ነውና፡፡ ከኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ.) በተላለፈው ዘገባ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም

«خير الناس أنفعهم للناس» ‹በላጩ ሰው ለሰው ጠቃሚ የሆነ ሰው ነው፡፡› ብለዋል፡፡ (ጦበራኒ ዘግበውታል፡፡)

ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ከመላካቸው በፊት ከእናታችን እመት ኸዲጃ ረዲየሏሁ ዐንሃ ጋር የንግድ ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ እሷ ገንዘብ ያላትና የተከበረች የመካ እመቤት ነበረች፡፡ የነቢዩን እውነተኝነት፣ ታማኝነትና የመልካም ሥነምግባር ባለቤት  መሆናቸውን ባወቀች ጊዜ ወደ ሻም አገር ከአገልጋዩዋ ጋር ሄደው በገንዘቧ እንዲነግዱላት ጠየቀቻቸው፡፡ ነቢዩም ሰላለሁ ዐለይህ ወሰለም መይሰራ ከሚባል አገልጋይዋ ጋር በመሄድ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ በማግኘት ተመለሱ ፡፡ ይህ ታማኝነታቸው  ነበር ኸዲጃ ነቢዩን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ለጋብቻ እንድትጠይቃቸው ያነሣሣት፡፡

ነቢያችን ስንፍናን፣ ሥራ ፈትነትንና ተቀምጦ መብላትን እጅግ አድርገዉ ያወግዙ ነበር፡፡ በቡኻሪ ዘገባ

مَا أَكَلَ أَحَدٌ طَعَامًا قَطُّ خَيْرًا مِنْ أَنْ يَأْكُلَ مِنْ عَمَلِ يَدِهِ وَإِنَّ نَبِيَّ اللَّهِ دَاوُدَ عَلَيْهِ السَّلَام كَانَ يَأْكُلُ مِنْ عَمَلِ يَدِهِ 

‹አንድ ሰው በእጁ ሠርቶ ከሚያገኘው የተሻለ በላጭ ነገር አይበላም፡፡ የአላህ ነቢይ ዳዉድ (ዐ.ሰ.) እጃቸው ሠርተው ካገኙት ይበሉ ነበር፡፡› በማለት የሥራና የላብ ዉጤት ጣፋጭ መሆኑን ያስተምሩ ነበር፡፡ የነቢዩ ሰሐቦች ለሁለቱም ዓለም ታታሪ ሠራተኞች ነበሩ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም          لَأَنْ يَحْتَطِبَ أَحَدُكُمْ حُزْمَةً عَلَى ظَهْرِهِ خَيْرٌ لَهُ مِنْ أَنْ يَسْأَلَ أَحَدًا فَيُعْطِيَهُ أَوْ يَمْنَعَهُ

 

‹አንዳችሁ በጀርባው እንጨት ተሸክሞ ማምጣቱ ሰው ለምኖ ከሚሠጠው አሊያም ከሚከለክለው ይሻልለታል ፡፡› መክረዋቸዋልና፡፡ ከሰሐቦችም መካከል ምርጥ የሚባሉት እነ ዐብዱረህማን ኢብኑ ዐውፍ እና ዑሥማን ኢብኑ ዐፋን ታላላቅ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡

ስለ ንግድ እና ነጋዴ አንዳንድ

ሐራም ነገርን መሸጥ

አንድ ነገር ሐራምነቱ የታወቀ ከሆነ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መልኩ መሸጥና ገንዘቡንም  መጠቀም ሐራም ነው፡፡  ያ ነገር የሚበላ ፣ የሚጠጣ፣ የሚለበስ ፣ የሚሠሩት ነገር አሊያም ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ሐራም ነገር መሸጡ የተከለከለ ስለመሆኑ ኢስላም ደንግጓል፡፡ መሸጡ ክልክል የሆነ ነገር ደግሞ ገንዘቡንም መዉሰድና መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡ ከሐራም  የሚገኝ ገቢን ለራስ መጠቀምም ሆነ ለሌላ አሣልፎ ስጦታ መስጠቱ አይበቃም፡፡  የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም

إن الله عز وجل إذا حرم أكل شيء حرم ثمنهُ. ‹ ኃሉና የተከበረው አላህ አንድን ነገር እርም ካደረገ ገንዘቡን እርም አድርጓል › ብለዋል፡፡ (አሕመድ እንደዘገቡት)

ከታማኙና እውነተኛው ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) በተላለፈው ዘገባ ‹የቂያማ ቀን የአንድ ባሪያ እግሮች አይንቀሳቀሱም ከአራት ነገሮች የተጠየቀ ቢሆን እንጂ፤ እድሜዉን በምን እንደጨረሠ፤ በእዉቀቱ ምን እንደሠራ፤ ሰውነቱን በምን ተግባር እንዳለቀ፣ ገንዘቡን ከየት እንዳገኘና ምን ላይ እንዳዋለ › የሚል ጥያቄ እንዳለብን ተነግሮናል ፡፡ እናም ከአሁኑ ለጥያቄዎቹ መልስ እናዘጋጅ፡፡ የመልሱንም ትክክለኛነነት እናረጋግጥ ፡፡ ልብ እንበል – ዛሬ ሥራ ነው ምርመራ የለም ፤ ነገ ደግሞ ምርመራ ነው ሥራ የለም ፡፡ በመሆኑም ስንሠራና ሀብት ስናፈራ በዘፈቀደ አንሰብስብ፤ ሐራም የገንዘብ ማግኛ መንገዶችን እንራቅ ፡፡

እያንዳንዱ ሐራም ነገር ዛሬ በባለቤቱ ላይ መጥፎ ጠባሳ አለው፤ የነገ ቅጣቱ ደግሞ የከፋ ነው፡፡ ሐራም የሚበላ የሚጠጣና በሐራም ያደገ በደለኛ ሰው ዱዓዑ ተቀባይነት የለውም፡፡  ዱዓዑ እንዲሰማለትና ምኞቱ እንዲሠምር የፈለገ የገንዘብ ምንጩ ከሐራም እንዳይሆን ተጠንቀቅ፡፡ በሐራም የተሠራች የዛሬዋ ትንሽ ነገር የነገውን ትልቅ ስኬት ልታሣጣ ትችላለችና ፡፡ ነቢያችን እንዲህ ይላሉ –

إن الله جميل يحب الجمال  ‹አላህ ቆንጆ ነዉ ቆንጆ ነገርን እንጂ አይቀበልም፡፡›

‹ከሐራም ያደገ ሰዉነት እሣት ለሱ በላጭ ነዉ፡፡› ይላሉ በሌላ ሐዲሣቸዉ ፡፡

መነፋፋቱንና ማደጉን አትዩ፡፡ በሐራም ያደገ ነገር ሁሉ ባዶና ውሸት ነው ጥንካሬ የለውም፡፡ መሠረቱም ደካማ ነው፡፡ ምሰሶውም ያረገረገ ነው፡፡ የሰዎችን በሐራም ነገሮች መወዳደር አይተን አንታለል፡፡ እነሱ እንደከበሩት ለመክበር ብለን መንገድ አንሣት፡፡ የነሱ አለመጠንቀቅ እኛን ከመጠንቀቅ አያግደን፡፡

يأتي على الناس زمان لا يبالي المرء ما أخذ منه، أمن الحلال أم الحرام

‹ በሰዎች ላይ ዘመን ይመጣል አንድ ሰው ገንዘቡ ከሐራም ይሁን ከሐላል የማይጨነቅበት› ብለዋል ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም፡፡ (ቡኻሪ እንደዘገቡት)፡፡ ዛሬ የምናየው ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉ ከዚህ የራቀ አይደለም፡፡›

ኢስላም ሐላል ነገሮች በግልፅ ደንግጓል፡፡ ሐራም ነገሮችንም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በመካከል ግን ሐላል ሐራምነታቸው በግልፅ ያልተለየ አጠራጣሪ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነሱን ከመዳፈር ይልቅ መፍራት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከመቅረብም ይልቅ መራቁ ነው ተመራጭ የሚሆነው፡፡ ሰሐቦች አንዲት ጉርሻ እንኳ ሐራም የበሉ እንደሆን እሷን ለማውጣት የማያደርጉት ጥረት የለም፡፡ ‹ለምን ከነፍሴ ጋርም አይሆንም አወጣታለሁ› ይሉ ነበር ታላቁ ሶሐባ አቡበክር አስስዲቅ ረ.ዐ. ፡፡

የሚያግራራን አላህ ያግራራለታል

አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ባሮቹን ሁሉ በፍትህና በመልካምነት አዟል፡፡ ፍትህ ደግሞ የስኬቶች ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ለነጋዴዎች ሲሆን ደግሞ ትልቁ ሀብት ነው፡፡ በንግድ ላይ እውነተኛነት፣ ፍትሃዊ መሆን፣ መጉዳትም ሆነ አለመጎዳት ፣ ለሰው ልጅ በጎ መዋልና ማግራራት ደግሞ ለራስ ደስታንና እርካታ ከአላህ (ሱ.ወ.) ዘንድ ደግሞ ዉዴታን ያጎናፅፋል፡፡ ማግራራት ሲባል በንግድ ወቅት ለአንድ እቃ ከተገቢው ዋጋ በላይ አለመጠየቅ፣ በቂ ገንዘብ የሌለውን ሰው አለማጨናነቅ ነው፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ዛሬም ሆነ ነገ ነገሮችን እንዲያገራለት የፈለገ ሰው አንድ ወንድሙ ‹የለኝምና ቀንስልኝ› ካለው ይቀንስለት፤ ጊዜ ስጠኝ ካለ ጊዜ ይስጠው፤ ተቸግሬያለሁ በዱቤ ስጠኝ ካለም ያግዘው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የገዛው እቃ ካልተመቸውና አልስማማው ካለ  መልስልኝ ብሎ ከጠየቀ ይመልስለት፣ ቀይርልኝ ካለም በመቀየር ይተባበረው፡፡ እናግራራ አላህ የሚያግራሩትን ይወዳልና፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡-

 رحم الله رجلا سمحا إذا باع وإذا اشترى وإذا اقتضى

‹ሲሸጥ፣ ሲገዛም ሆነ ሲፈርድ የሚያልፍ /የሚያግራራ/ የሆነን ሰው አላህ ይዘንለት› (ቡኻሪ እንደዘገቡት)

በሌላም ሐዲሣቸዉ  ‹የጨነቀውን ሰው ያገራለት አላህ የዱኒያና የአኪራ ጉዳዮችን ያገራለታል ፡፡› ብለዋል፡፡

በደልን እንጠንቀቅ

ትንሽ ይሁን ትልቅ ሰዎችን አላግባብ የምንጎዳበት እያንዳንዱ ነገር ሁሉ ዙልም /በደል/ ነው፡፡ በደል ደግሞ ዉጤቱ የከፋ ነው፡፡ በልብ፣ በቀብርም ሆነ በቂያማ ቀን ጨለማን ያወርሣል፡፡ ‹በደልን ፍሩ ፤ በደል የቂያማ ቀን ድርብርብ ጨለማ ነዉና› ይላሉ ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም፡፡

የቂያማ ቀን ጨለማ ነውና ማንኛዉም ሰው የተሟላ ብርሃንን ይፈልጋል፡፡ የዚያን ቀን ብርሃን ያላቸውና የሌላቸው ይኖራሉ፡፡ ያላቸው ሊኖራቸው የቻለው በዱኒያ ላይ ቆይታቸው ወቅት አላህን በመፍራታቸውና ከበደልም በመራቃቸው ነው፡፡  ዛሬ ገንዘቡ ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ የተወሠደበት ሰው ነገ ከወሠደበት ሰው በላይ አትራፊ እሱ ነው፡፡ ምክኒያቱም በነገው ቀን የፍርድ ዉሳኔ ገንዘብን በገንዘብ መመለስ ሣይሆን መልካም ሥራን ከበዳይ በመንጠቅና ለተበዳይ በመስጠት ነው የሚካሠው፡፡ ዕለተ ትንሳኤ ገንዘብ ሳይሆን መልካም ሥራ የሚያስፈልገበት አደባባይ ነው፡፡

ለኛ እጅጉን አዛኝ የሆኑት ነቢያችን እንዲህ በማለት ይመክሩናል

من كانت عنده مظلمة لأخيه فليتحلل منها، فإنه لا دينار ولا درهم من قبل أن يأخذ لأخيه من حسناته، فإن لم يكن له حسنات أخذ من سيئات أخيه فطرحت عليه“.

‹ወንድሙን የበደለ ሰው ዲናርም ሆነ ድርሃም የሌለበት ቀን ከመምጣቱና መልካም ሥራዉ ተወስዶ መልካም ሥራ ከሌለውም የወንድሙ መጥፎ ሥራ በሱ ላይ የሚጫንበት ቀን ከመምጣቱ በፊት በደሉን ዛሬዉኑ ይካስ፡፡› (ቡኻሪ ዘግበውታል)

የነገዉን ከባድ ፈተና ለማለፍና ጀነት ለመግባት ገንዘብ ሣይሆን ከምንም በላይ መልካም ሥራዎች ያስፈልጉናል፡፡ ዛሬ የምናገኘው ተራ ጥቅም ነገ ከሚወሰድብን በምንም መልኩ የተሻለ አይሆንም ፡፡

ማታለልና ማጭበርበር

አንድ ቀን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም  ለምግብ በሚውልና በሚሸጥ (ክምር) እህል ዘንድ አለፉ፡፡ እጃቸዉንም ወደ ክምሩ በሰደዱ ጊዜ በዉስጡ እርጥበት አገኙ ‹ ይህ ምንድነዉ የዚህ እህል  ባለቤት ሆይ !› በማለት ጠየቁ፡፡ ‹ዝናብ አግኝቶት ነው› አለ የእህሉ ባለቤት፡፡ ‹ ታዲያ ሰዎች እንዲያዩት ለምን እላዩ ላይ አላደረግክም ?› አሉት፡፡ በመቀጠልም ‹ ያታለለን ከኛ አይደለም ፡፡› በማለት ተናገሩ ፡፡

እነኚህንና የመሣሠሉት ዓይነት ማታለሎች ዛሬ በማህበረሰባችን ዉስጥ በዝተዋል፡፡ ኦሪጅናል  ያልሆነዉን እቃ ነው ብሎ ለማሣመን መሞከር፣ ዐይብ እንዳለበት እያወቁ ሸፋፍኖ መሸጥ፣  ሁለተኛውን ደረጃ ዕቃ አንደኛ ነው በማለት መዋሸት እነኚህ ሁሉ ከማታለል የሚመደቡ ናቸው፡፡

በየትኛውም መልኩ ሰዎችን ማታለልን ሸሪዓችን አይደግፈውም፡፡ ሰዎችን በማምታታት የሚገኘው ገንዘብ የቱን ያህል ቢቆለልም አንድ ቀን መናዱ አይቀርም፡፡  ስለዚህ ለጥቂት ዓለማዊ ጥቅሞች ብለህ ከጌታችን አንጣላ፡፡ ደግሞም አንዋሽ፤ ዉሸት እጅግ የተጠላ ባህሪ ነውና ‹ ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው፤ አይዋሸውም፡፡› ብለዋል ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዉሸት የንፍቅና ምልክት ነዉ ፡፡ ወንድምህ እያመነህ አንተ የምትዋሸዉ ከሆነ ትልቅ ክህደት ነው፡፡ እዉነትን እያወቁ መደበቅ ፤ ለሌሎች አለማሰብ ፣ ስግብግብነትና የራስን ጥቅም ብቻ ከማሣደድ የሚመነጭ ነው፡፡ ቢጎዳንም እዉነትን እንናገር፣ ቢጠቅመንም ዉሸትን እንተው፡፡ እቃችን የሌላትን ጥራት አላት አንበል ፣ ጉድለቷን አንደብቅ ፤ ነዉሯን አንሸፋፍን ፤ እንከኗን አናለባብስ ፡፡ ያኔ አላህ ንግዳችንን ይባርክልናል፤ እውነትን በመናገራችን ይክሰናል፡፡ የአላህ ነቢይ እንዲህ ብለዋል

‹ ገዥና ሻጭ እስካልተለያዩ ድረስ (መሻሻጣቸዉን የማፍረስም ሆነ የማፅደቅ) ምርጫ አላቸዉ ፡፡ እውነትን የተናገሩና ሁሉን ነገር ግልፅ ያደረጉ እንደሆነ መሻሻጣቸዉ /መገበያያታቸዉ/ ይባረክላቸዋል ፡፡ የደበቁና የዋሹ እንደሆነ ግን የግብይታቸዉ በረከት ይነሣል፡፡›

ሥፍርና ሚዛን ማጉደል ሌላው ሰዎችን የማታለያ መንገድ ነው፡፡ ይህም ሆነ ብሎ አሊያም በቸልተኝነት ‹ምንም አይደል፣ ብዙም ለዉጥ የለዉም › በማለት ሊሆን ይችላል ፡፡ ሐራም ነገር ትንሽ ቢሆንም ሐራምነቱን አይለቅም ፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ በብዙ የቁርኣን አንቀፆች ላይ ከዚህ ዓይነቱ እኩይ ድርጊት አስጠንቅቋል ፡፡ ወይሉን ሊልሙጠፍፊን / ለሰላቢዎች ወየዉላቸው፣ እነዚያ › ( አል-ሙጠፍፊን ፡1-3) የሚለው አንዱ ነው፡፡ በሌላ አንቀጽም

‹ ስፍርን ሙሉ ከአክሳሪዎችም አትሁኑ ፤ በትክክለኛው ሚዛንም መዝኑ፤ ሰዎችንም ነገሮቻቸዉን አታጉድሉባቸው፤ በምድርም ላይ አጥፊዎች ሆናችሁ አታበላሹ ፡፡ › ( ሹዐራእ ፡  181-183 )

ከላይ በተገለፁት አንቀፆች አላህ ለነዚያ ለራሣቸዉ ሲሰፍሩ የሚሞሉትን ለሌሎች ሲሰፍሩ የሚያጎድሉትን አስጠንቅቋል ፡፡ ታላቁን ቀን አይፈሩም እንዴ ! ሲልም ይጠይቃል ፡፡  ሁለት ነገሮችን ልብ እንበል-

አንደኛ – አንድ ሰው የእቃዉን ምንነት መደበቁ ፤ ኦሪጅናል ያልሆነዉን ነው ማለቱ ፤ የሌላትን መናገሩና ቃላትን ማሠማመሩ፤ ሥፍርም ሆነ ሚዛን ማጉደሉ ቀድሞ በተፃፈው ርዝቁ ላይ ምንም አይጨምርለትም ባይሆን ድፍርስ ውሃ ከንፁህ ጋር ሲቀላቀል እንደሚያደፈርሰው ሁሉ ሐላል ከሆነው ሀብቱ ጋር ሲቀላቀል ያጠፋዋል በረከትን ይነሣዋል፡፡ ሰደቃ ከገንዘብ እንደማያጎድል ሁሉ ክህደትና ማታለልም በገንዘብ ላይ አንዳች ነገር አይጨምሩም፡፡

2ኛ- የአኺራ ትርፍ ከዱኒያዉ እጅግ የተሻለ መሆኑን አንዘንጋ ፡፡ የዚህች ዓለም ጥቅም የሰው ልጅ እድሜ ከፍ ባለ ቁጥር ይቀንሣል ፤ በደሏና ጥፋቷ ፤ ሀጢአትና ወንጀሏ ግን ሸክም በመሆን አብሮ አኺራ ይወርዳል፡፡ ታዲያ ዐቅለኛ የሆነ ሰው ትንሹን ነገር ከትልቁ፣ ተራውን ነገር ከበላጩ እንዴት ይመርጣል ያስቀድማል ፡፡

መሀላችሁን ጠብቁ

የአል-ማኢዳህ ምዕራፍ ቁ -93 ላይ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ‹ መሃላችሁን ጠብቁ › ይለናል፡፡ መማል የግድ ካልሆነ በስተቀር ለመማል ብቻ መማል ተገቢ አይደለም፡፡ ዛሬ ለትንሹም ሆነ ለትልቁ ነገር መሐላ የተለመደ ሆኖ እናያለን ፡፡ በመሀላ አለመጠንቀቅ ለአላህ ሥም  ክብር አለመስጠት ነው፡፡ አንድን ነገር ለመሸጥ መሀላ የግድ መሆን የለበትም ፡፡ ሙስሊም ሻጭ እውነትን መናገር ገዥውም ሻጭን ማመን ግድ ይለዋል ፡፡  አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ በውሸት በስሙ የሚነግድን ሰው ከባድ የሆነ ዛቻ አዉርዶበታል ፡፡ አሊ ዒምራን  77 ፡፡

የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም በሐዲሣቸዉ እንዲህ ብለዋል ‹ የቂያማ ቀን አላህ ሦስት ዓይነት ሰዎችን አያናግራቸውም ፤ ወደነርሱም አይመለከትም ፤ ከመጥፎ ወንጀላቸውም አያጠራቸውም ፤ ለነሱም አሣማሚ ቅጣት አለ› ይህንኑ ሦስት ጊዜ ደጋግመው ተናገሩ ፡፡ አቡዘርም ረዲየሏሁ ዐንሁ ‹ ባዶ ሆኑ ከሠሩ፤ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እነሱ እነማናቸው › በማለት ጠየቀ ፡፡ እርሣቸውም ‹ ልብሱን መሬት ላይ የሚጎትት፣ ጉረኛ / በሠጠዉ ነገር የሚመፃደቅ/ ፣ በውሸት መሃላ እቃውን የሚሸጥ › በማለት መለሱ ፡፡

በሌላም ሐዲሣቸው   (الحلف منفقة للسلعة، ممحقة للبركة)) ‹መሐላ እቃን ያስገኛል፤ በረከትን ግን ያጠፋል፡፡› ብለዋል ፡፡

መጨራረት

ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው፣ በምንም መልኩ አይበድለውም፣ ሊበድለውም አይገባም፡፡ ከወንድማማችነት ሐቆች መካከል አንድ ሙስሊም ለራሱ የሚወደውን መልካም ነገር ለወንድሙ መውደዱ ነው፡፡  የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ‹ ወደ ገበያ የሚመጡትን (ነጋዴዎች) መንገድ ላይ አትጠብቁ፡፡ አንዳችሁም በሌላኛው ገበያ ለይ አይሽጥ፡፡›

አንዱ በሌላኛዉ ገበያ ላይ መሸጥ ማለት- አንደኛው ሊሸጥ በመደራደር ላይ እያለ ሌላኛዉ አይጥራው፣ ታልቃ አይግባ፣ ከሸጠ በኋላም ቢሆን እኔ ከሱ ባነሠ ዋጋ እሸጥልሃለሁ በማለትና በመሣሠሉት ቃላት ሀሳቡን አያስለውጠው ማለትን ያካትታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ነጋዴዎች የሀገሬውን ዋጋ የማያውቅን ሰዉ በርካሽ ዋጋ ለመግዛት ብለዉ ቀድመው መንገድ ላይ በመውጣት እንዳይገዙት ያሣስባሉ፡፡ ለመግዛት ሀሳቡ ሣይኖር በእቃ ላይ ዋጋ ጨምሮ ሌላውን ማሣሳትም ሌላኛው ስህተት ነዉ ፡፡

የሰላት ነገር

ሰላት በኢስላም ውስጥ ታላቅ ቦታ አላት፡፡  ከአምስቱ የእስልምና ማእዘናት አንዷ ስትሆን የሃይማኖቱም ምሠሦ ናት፡፡ ይህ ከመሆኑ ጋር በንግድ ምክኒያት የሰላትን ነገር ችላ የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ዱኒያዊና ዲናዊ ነገሮች አንድ ላይ የመጡ እንደሆን ሁሌም የዲን ጉዳይ ይቀድማል፡፡ ምክኒያቱም ዱኒያ ጠፊና ጊዜያዊ ስትሆን አኺራ ደግሞ ዘላለማዊና ቋሚ አገር ናትና፡፡

አላህ በአኺራ ያዘጋጀለትን ድግስ በወጉ የተገነዘበ በዚህኛው ዓለም ጥቅም አይታለልም፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ በንግድና በሌላም ምክኒያት ከሰላት የማይዘናጉት ትጉሃን ባሮቹን ያሞካሻል፡፡ (ሱረቱ ኑር  36- 37) ፡፡

ምእመናን ከሥራ አልተከለከሉም፡፡ ይሸጣሉ ይገዛሉ፤ ነገር ግን አላህ ግዴታ ያደረገባቸው ነገር የመጣ እንደሆን ከሱ የሚያስቀድሙት ነገር የለም፡፡ ሰሐቦች ሰላት ሲደርስ አሊያም ሙአዚኑ ወደ መስጊድ የተጣራ እንደሆን ትርፉ የቱን ያህል የበዛ ቢሆን እንኳ የሱቃቸውን በር ይዘጋሉ፡፡ እኛም የነዚያን ደጋጎች ፈለግ እንከተል፡፡ በአላህ (ሱ.ወ.) በመተማመን ወደ መስጊድ እንምጣ፡፡ ርዝቃችን የትም እንደማያመልጥ እርግጠኛ እንሁን፡፡ ከአምልኮ ተግባራት ሁሉ ከግዴታ ነገሮች በላይ ወደ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ የሚያቀርብ ምንም የለም፡፡ ሰላት ዋጋዋ ከባድ ነው፡፡ በቂያማ ቀን የሰው ልጅ መጀመሪያ የሚጠየቀው ከሷ ነው፡፡ እሷ ካማረች ሁሉም ነገር ያምራል ከተበላሸች ደግሞ ዉድቀት ይበዛል – አላህ ይጠብቀን ፡፡ አምላኩ ግዴታ ያደረገበትን የተወጣ ሰው ትርፉ የበዛ ነው፡፡ መንፈሱ ይረካል ፣ ዉስጡ ይሰክናል ፣ ደረቱ ይሠፋል ፡፡ ወደ መስጊድ ስንገባ ‹ ጌታዬ ሆይ ! የእዝነትህን በር ክፈትልኝ› ስንወጣ ደግሞ‹ ጌታይ ሆይ ! ከችሮታህ እለምንሃለሁ› የማለታችን ሚስጢሩ ምን ይሆን!፡፡

በራእ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ.) የጁሙዓ ሰላት ከሰገደ በኋላ በመስጊድ በር ላይ ይቆምና ‹ጌታዬ ሆይ ! ጥሪህን ተቀብዬ መጥቻለሁኝ ፤ ግዴታ ያደረግክብኝንም ሰላት ሰግጃለሁ ፤ እንዳዘዝከኝ በምድርህ ላይ ተበተንኩ፤ አንተ በላጩ ለጋሽ ነህና ከችሮታህ ለግሠኝ ፡፡› ይል ነበር ፡፡

አላህ ለሚወደው ነገር ሁሉ ይወፍቀን፡፡

WWW.ALIFRADIO.COM

muslim-greetings1ሙስሊም በሙስሊም ወንድሙ ላይ ሐቅ አለው፡፡ ይህንን ሐቅ መወጣት በማንኛውም ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው፡፡ በተለያዩ ነቢያዊ ሐዲሦች ዉስጥ ከተነገሩ አንድ ሙስሊም በሌላኛው ላይ ካለው ሐቆች /መብቶች/ መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-

 • ሰላምታን ማቅረብ /አሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላህ ወበረካቱህ ማለት/ አንድ ሙስሊም ሙስሊም ወንድሙን በሚያገኝበት ጊዜ ቢያውቀውም ባያውቀውም ሰላምታ ሊያቀርብለት ይገባል፡፡ በሰላምታ መቅደምም ተወዳጅ ድርጊት ነው፡፡
 • ሰላምታን መመለስ – ሰላምታ የቀረበለት ሰው ደግሞ ሰላምታውን በተመሳሳይ አሊያም በተሻለ መልኩ መመለስ ይኖርበታል፡፡ ሰላምታ መመለስ ግዴታ ነው፡፡
 • ያስነጠሰን ማስደሠት (የርሐምከላህ ማለት) – ማስነጠስ ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ ከጭንቀት በኋላ ርግበት፡፡ ስለሆነም ሙስሊም በዚህን ጊዜ ጌታውን ያመሰግናል፡፡ አልሐምዱ ሊላህ በማለት፡፡ አጠገቡ ያለ ሙስሊም በዚህ ሊደሰትለትና የርሐምከላህ (አላህ ይዘንልህ) ሊለው ይገባል፡፡
 • የታመመን መጠየቅ – የታመመ ሰው መጠየቅ አለበት፡፡ ሙስሊም ሲታመም ወንድሞቹ ሊጎበኙት፣ በፈውስ እና በአላህ እዝነት ሊያበረታቱት እና ዱዓእ ሊያደርጉለት ይገባል፡፡
 • ለጥሪው ምላሽ መስጠት – አንድ ሙስሊም ሰርግ፣ ሰደቃ አሊያም ሌላ የደስታም ይሁን ሌላ ዝግጅት ኖሮት በዝግጅቱ ላይ እንድንገኝለት የጋበዘን እንደሆነ መገኘት ግድ ነው፡፡
 • የሞተ እንደሆነ ጀናዛውን መከተል /ወደ መቃብር መሸኘት – መቃብር ወደመጨረሻው ዓለም መሸጋገሪያ ሥፍራ ነው፡፡ የሞተ ሰው ምድር ላይ ያሳለፈውን ሥራ ይዞ አላህ (ሱ.ወ.) ፊት ይቀርባል፡፡ ስለሆነም ሙስሊሞች ወንድማቸው የሞተ እንደሆነ አጥበው፣ ከፍነውና ሰግደውበት የአላህን (ሱ.ወ.) እዝነትና ምህረትም ለምነውለት ወደማይቀረው ቤቱ ሊሸኙት ይገባል፡፡
 • የማለን መሀላውን ማፅናት – አንድ ሙስሊም ያደርግልኛል ብሎ በኛ ተማምኖ የማለ እንደሆነ ልናሳፍረው አይገባውም፡፡ መሀላውን ልናፀናለት ይገባል፡፡
 • የተበደለን ማገዝ – አንድ ሙስሊም የተበደለ እንደሆነ በቻልነው ሁሉ ከጎኑ መቆም ይኖርብናል፡፡ ይህም እሱ ከኛ ላይ ያለው አንድ መብቱ ነው፡፡ የበደለ እንደሆነም እንዳይበድል ልናስታግሰው ይገባል፡፡
 • የቸገረውን ሰው ከችግሩ ለማውጣት መረባረብ፣ የተጨነቀንም ከጭንቀቱ መገላገል፡፡ ሙስሊምን ከጭንቀቱና ከችግሩ የገላገለን ሰው አላህ በቂያማ ቀን ከችግር እንደሚገላግለው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ተናግረዋል፡፡
 • ምክር ለሚያስፈልገው ሰው ማማከር – ሙስሊም ወንድማችን ያማከረን እንደሆነም ልናማክረው ግድ ይላል፣ ያሳሰበው ነገር ካለም መላ ልንፈልግለት ይኖርብናል፡፡
 • ያጠፋን ነውሩን መሸፈን – አንድ ሙስሊም ያጠፋ እንደሆነ ጥፋቱን አደባባይ ማውጣትና ማዋረድ ተገቢ አይደለም፡፡ ገመናውን ልንሸፍንለትና በሚስጢር ልንመክረው ይገባል፡፡
 • ሙስሊም አለመናቅ – አላህ መልዕክተኛ ለአንድ ሰው ክፋቱ ሙስሊም ወንድሙን መናቅ በቂ ነው፡፡› ብለዋል፡፡ አንድ ሙስሊም በአላህ በማመኑ ብቻ ትልቅ ክብር አለው፡፡
 • ከዚህም ሌላ ሙስሊም በሙስሊም ወንድሙ መቅናትና መመቅኘት የለበትም፡፡ በደል፣ ጥላቻና ኩርፊያንም ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ ከሶስት ቀን በላይም ሊያኮርፈው አይገባም፡፡ በመልካም ነገርና በአላህ ፍራቻም ሊያስታውሰው ይገባል፡፡ እነኚህና የመሳሰሉት ሁሉ በአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሐዲሥ የተጠቀሱ ሐቆች /መብቶች/ ናቸው፡፡

www.alifradio.com

የደም ጉዳይ

ሁላችንም የሰው ልጆች የአንድ አባትና እናት ልጆች ነን፡፡ የአደምና ሀዋ፡፡ አንዲት ሰፊ አገርም አለን፡፡ እሷም መሬት/ምድር ትባላለች፡፡ ያለ ክፋት፣ ጥላቻና ምቀኝነት ስንሆን ለሁላችንም ትበቃለች፡፡ የሁሉንም አስተሳሰብና አመለካከት ባለቤቶች ሰፋ ባለ መልኩ ትይዛለች፡፡ ሆነብለን ካልተገፋፋን በስተቀር አዎን ምድር በቂያችን ናት፡፡ በነቢዩ ዘመን የታላቁ ነቢይ መናገሻ በሆነችው የመዲና ከተማ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖችና አይሁዶች ለዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ እንዴት ከተባለ – በሃይማኖት ማስገደድ ስለሌለ፣ ወደ ቀናው የእስልምና መንገድም ጥሪ የሚደረገው በጥበብና በመልካም ምክር ስለሆነ፣ በሃይማኖት ጉዳይ ሲከራከሩም እጅግ ባማረ ሥነምግባር ስለሆነ ነበር፡፡

ዛሬ ላይ ግን በዓለም ላይ የሚታየው የጊዜው የፈተና ዳመና፣ የአንዳንድ ሙስሊሞች ጥፋት፣ የዓለም ፖለቲካ ተንኮልና የሚዲያ ግነት ተደምሮበት ሙስሊሙ በዲኑም ሆነ በዱንያው ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ በማህበራዊ ኑሮም ከዚህም ከዚያም ለውግዘትና ለጥርጣሬ ዳርጎታል፤ መልካም ስሙንም አጠልሽቷል፣ ኢስላም ማለት ‹ሰላም› ነው የሚለውንም አባባል ጥያቄ ዉስጥ ከቶታል ፡፡ የሽብር.. ሥም ሲነሳ ሙስሊም አብሮ ይነሳል፡፡

እስልምና ገና ከጅማሮው የደምን ጉዳይ አክብዶታል፡፡ ከእስልምና ትላልቅ ዓላማዎች መካከል አንዱ የሰውን ልጅ ነፍስ መጠበቅ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡

አላህ ሱብሐኑ ወተዓላ የሰውን ልጅ ምድር ላይ ያስገኘው ለመልካም ዓላማ ነው፡፡ በዋናነትም አምልኮና የምድር ልማት፡፡ ይህን መልካም ዓላማውን ይፈጽሙ ዘንድ አላህ (ሱ.ወ.) የሰውን ልጆችን በምድር ላይ ምትክ እንደሚያደርግ ለመላኢኮች በገለፀ ጊዜ መላእክት ጠየቁ‹ ‹የሰው ልጅ በምድር ላይ በጥፋት ይሄዳል፣ ደምንም ያላግባብ ያፈሳል› በማለት፡፡ (የአል-በቀረህ ምዕራፍ ቁ-30) አላህም እነርሱ የማያውቁት ነገር እንዳለ ለመላእክቱ ነገራቸው፡፡ ብቻ ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር የሰው ልጅ ነፍስ የተከበረች መሆኗንና በግድያ ወንጀል ፍጡራን ሁሉ እንዴት እንደሚሸማቀቁ ነው፡፡

በኢስላም – ግድያ የወንጀሎች ሁሉ የበላይ ከሆነው በአላህ ከማጋራት የ(ሺርክ) ወንጀል ቀጥሎ ትልቁ ወንጀል ነው፡፡ ቁርኣን አንዲትን ነፍስ ያላግባብ መግደልን ሰዎችን በሙሉ እንደመግደል ነው ብሎታል፡፡ (አል-ማኢደህ፡ 32) ከዚህም ሌላ በርካታ ቦታዎች ላይ ከባባድ ማስጠንቀቂያዎችን አስተላልፎበታል፡፡

የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከእጅግ አደገኛና አጥፊ ወንጀሎች መካከል ሁለተኛ ላይ ቆጥረውታል፡፡ ነፍስን መግደል የሚያሳድረውን ትልቅ የሥነልቦና ተጽእኖ በሚገልፀው ሐዲሣቸው ደግሞ እንዲህ ይላሉ ‹አንድ ሙስሊም ሁሌም ሰላማዊና የተረጋጋ በሆነ ህይወት ውስጥ ነው የሚኖረው፤ አግባብ ባልሆነ መልኩ የሰውን ልጅ ደም እስካላፈሰሰ ድረስ፡፡› ብለዋል፡፡ በርግጥም የሰው ልጅ ነፍስ ትልቅ ዕዳ ናት፡፡ በሄደበት ሁሉ ገዳይን ትከተላለች፡፡

ሌላም እናክል – ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ‹በዕለተ ትንሳኤ በሰዎች መካከል ፍርድ የሚሰጠው በደም ጉዳይ ነው፡፡› ብለዋል፡፡ ይህም የጉዳዩን ክብደት የሚያሳይ ነው፡፡

እናም ከሰው ልጅ ደም አንፃር እስልምና ያለው አቋም በመጠኑ ይህን ይመስላል ለማለት ነው፡፡ እግረመንገዳችንንም እስልምና ከሰው ልጅ ደም አንፃር ያለውን እይታ በተመለከተ በተለይ ሙስሊም ባልሆኑት ዘንድ የተስፋፋውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር ከሙስሊሙ ብዙ ብዙ እንደሚጠበቅ ለማስታወስ ነው፡፡

#አሊፍ ራዲዮ

ኪራይ ሰብሳቢነት

የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.)  በሐዲሣቸው እንዲህ ብለዋል፡-

‹አንድን ሰው ለሥራ ቀጥረንና ሲሳይ (ደሞዝ) ቆርጠንለት ከዚያ ዉጭ የነካ እንደሆነ ስርቆሽ ነው፡፡›

ኢስላም አስተምህሮው በእጅጉ አስደናቂ የሆነ ሃይማኖት ነው፡፡ ሚዛናዊነቱ ከግርምትም በላይ ነው፡፡ ከኢስላም ትላልቅ መርሆች መካከል አንዱ ማንኘውም ሰው መጉዳትም ሆነ መጎዳት እንደሌለበት ማወጁ ነው፡፡ በአንድ መሥሪያ ቤትም ሆነ የግለሰብ ቤት የተቀጠረ ሰው የተቀጠረበትን ነገር ኃላፊነት ባለው መልኩ መወጣት ይኖርበታል፡፡ ሥራውን ማክበርና ተስማምቶ የገባበትንም ዉል ማክበር ግድ ይለዋል፡፡ ሙስሊሞች ለዉሎቻቸው ታማኞች ናቸው፡፡  አንድ ሰው ከተቆረጠለት ደሞዝ ዉጭ የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር አግባብ ባልሆነ መልኩ የተቀጠረበትን የግለሰብም ሆነ የተቋም ገንዘብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ የሚነካ፣ የሚወስድ፣ የሚመዘብር ከሆነ በርግጥም ሰርቋል ማለት ነው፡፡ ስርቆት ደግሞ በእስልምና ከባድ ወንጀል ነው፡፡ መስረቅ ሲባል ደግሞ ከገንዘብ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በቀን ለ10 ሰዓታት ሊሰራ ተስማምቶ የተቀጠረበትን መሥሪያ ቤት የሥራ ሰዓት የማያከብር ከሆነም እንደስርቆሽ ይቆጠራል፡፡ አርፍዶ የሚገባ ከሆነም እንደዚያው ነው፡፡ ሙስና አሊያም ኪራይ ሰብሳቢነት ልንለው እንችላለን፡፡

አላህ (ሱ.ወ.) በቁርኣኑ የሰውን ገንዘብ ያለ ሐቅ እንዳንበላ አስጠንቅቆናል፡፡ የሰው ሀቅ ከባድ ነው፡፡ በዕለተ ትንሳኤ መልካም ሥራን ሊያስነጥቅ ይችላል፤ የሌላን ሰው ወንጀል እስከማሸከም ይደርሳል፡፡ እና ጉዳዩን በቀላሉ ባንመለከተው ይበጃል፡፡

www.alifradio.com

ዘረኝነት በኢስላም

ኢስላም የህዝቦች ሁሉ ነፃ አውጭ ሃይማኖት ነው፡፡ ፍጡራንን ከባዕድ አምልኮ ወደ ታላቁ አምላክና ፈጣሪያቸው ወደሆነው አምልኮ ነፃ ሊያወጣ ነው የመጣው። በህዝቦች መካከል ሰፍኖ የነበረውን በፆታ፣ በመደብና በዘር የእኔ እበልጣለሁ እሻላለሁ ፉክክርን ሊገረስስ ነው የታወጀው።

አዎን — ያኔ ከኢስላም በፊት ዐረብ የሆነው ወገን ዐረብ ካልሆነዉ እንደሚበልጥ በኩራት ይናገር ነበር፣ ነጩ የጥቁር የበላይ እንደሆነ አድርጎ ይፎክር ነበር፣ ከፊሉ ቡድን በከፊሉ ይስቅ ይሳለቅ ነበር። ኢስላም ሲመጣ ግን ይህን በጠባብ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተውን የሰዉ ልጆች አመለካከት ተቃወመ፡፡ በአንድ ነገር ሲቀር የሰዉ ልጆች ሁሉ በአላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ፊት እንደ ማበጠሪያ ጥርስ እኩል መሆናቸውንም አስተማረ፡፡ የመበላለጫቸው መመዘኛ ለአላህ (ሱ.ወ.) ያላቸዉ ፍራቻ /ተቅዋ/ ብቻና ብቻ ነው።

አላህ (ሱ.ወ.) በተከበረዉ ቁርኣኑ ዉስጥ እንዲህ ይላል –

يأيها الناس إنا خلقناكم من ذكر وأنثى وجعلناكم شعوبا وقبائل لتعارفو إن أكرمكم  عند الله أتقاكم إن الله عليم خبير

 “ እናንተ ሰዎች እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፤ ትተዋወቁ ዘንድም ነገዶችና ጎሣዎችም አደረግናችሁ፤ በላጫችሁ አላህ ዘንድ ይበልጥ አላህን  ፈሪያችሁ ነው፤ አላህ አዋቂ (የዉስጥ ሚስጢራትንም) ጠንቅቆ አዋቂ ነው።” (አል-ሑጁራት፡ 13)

አላህ (ሱ.ወ.) ሰዎችን በዘርና በጎሣ የመከፋፈሉ ሚስጢር ይተዋወቁ ዘንድ ነው፡፡ አንደኛው በሌላኛው ላይ እንዲኩራራ ወይም እንዲመፃደቅ አይደለም፡፡

ነቢዩም ሰለላሁ ዐለይህ ወሰለም ‘እኛ ከሌላው ብሄር እንሻላለን’ ብለው ለሚኩራሩ ወገኖች ሁሉ መልስ አላቸው ‘ሁላችሁም የአደም ልጆች ናችሁ አደም ደግሞ ከአፈር ነው፡፡ ’ በማለት መለስ ብለው መነሻቸውን እንዲያስተውሉ ይመክራሉ፡፡ በርግጥም የሰዉ ልጅ  በዘር፣ በሀብት፣ በእውቀት በመልክም ሆነ በሌላ የሚኩራራውና የሚፎክረው መነሻው አፈር መሆኑን ባለማስተንተኑና ጠንቅቆ ባለማወቁ ይመስላል።

ሙስሊሙ ማኀበረሰብ አንድ ህዝብ ነው፡፡ አላህ በቁርኣኑ

إن هذه أمتكم أمة واحدة وأنا ربكم فاعبدون

‹ይህች አንዲት መንገድ ስትሆን በርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፡፡ እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ፡፡› ብሏል፡፡

እስልምና ከለገሰን ምርጥ እሴቶች መካከል ሀገርና ብሄር ሳይገድበው ሙስሊም ለሙስሊም ወንድም መሆኑ ነው፡፡ ኢስላማዊ ወንድማማችነት ከየትኛውም ትስስር በላይ ነው፡፡ ለዚህም ነው በነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የኖሩት ዐረብ ያልሆኑ ሙስሊም ሶሐቦች ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ዘንድ ትልቅ ከበሬታና ዉዴታ የነበራቸው፡፡ ቢላል ሐበሻዊ፣ ሰልማን ፋርሳዊ፣ ሱሀይብ ሩማዊ ነበር፡፡ ሆኖምግን ለትልቅነት መስፈርቱን እምነትና የአላህ ፍራቻ ያደረገው እስልምናችን ከከሃዲያን   ዐረቦች በላይ አላቃቸው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ስለ ሰልማን ሲናገሩ ‹ሰልማን ከኛ ነው፡፡ ከቤተሰባችንም ነው፡፡› ብለዋል፡፡ ቢላልን በሙአዚንነት መርጠዋል፡፡ ዑመር (ረ.ዐ.) ስለ ቢላል ሲጠቅሱ ‹አቡበክር አለቃችን ነው፡፡ አለቃችንን (ቢላል)ን ነፃ አውጥተዋል፡፡› ብለዋል፡፡

ነቢያችን በዘር መመፃደቅን አውግዘዋል፡፡ በዘር መኩራራት ከቀደምት የመሃይማን ድርጊቶች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሐዲሣቸው ‘ሁለት ነገሮች – በዘር መሠዳደብና በሙታን ላይ ዋይታ በአላህ የመካድ መገለጫዎች ናቸው።’ ብለዋል። አሳዛኙ ነገር ዛሬም ቢሆን ከሙስሊሞች መካከል በቀደምት የጃሂሊያ ባህሪዎች የተጠመቀ ሰው ቁጥሩ ቀላል አለመሆኑ ነው።

እስልምናችን የፍትህና የእኩልነት ሃይማኖት ነው፡፡ አስተምህሮዉም ‹የሰው ልጆች ሁሉ እንደማበጠሪያ ጥርስ እኩል ናቸው› የሚል ነው፡፡ በዚህም አመለካከቱ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችን ሁሉ ይቀድማል፤ የእኩልነት የነፃነትና የፍትህ አቀንቃኞችን ሁሉ ያስከትላል።

ዘረኝነት ከሰዉ ልጅ አስቀያሚ በሽታዎች መካከል አንዱ ነዉ ። ‘እኔ ካንተ እበልጣለሁ ’ የምትለው ቃል ኢብሊስ ከአላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ እዝነት እንዲባረር ምክኒያት የሆነች የኩራትና የምቀኝነት ቃል  ናት።

አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ የሰው ልጆችን የተለያየ ቋንቋና ቀለም ባለቤቶች አድርጎ መፍጠሩ ለተጨማሪ ተፈኩር የሚጋብዝ እንጂ አንዱ በሌላኛዉ ላይ እንዲኩራራና እንዲናቆር አይደለም  ።

ላይ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ይላል፡-

ومن آياته خلق السموات والأرض واختلاف ألسنتكم وألوانكم إن في ذالك لأيات للعالمين   

“ ሰማያትንና ምድርን መፍጠሩ ቋንቋዎቻችሁና ቀለሞቻችሁ መለያየቱ ከተዓምራቱ ነዉ ። በዚህ ዉስጥ ለአዋቂዎች ተዓምራት አሉ ።” (አር-ሩም ፡22)

ስለሆነም ማንኛውም ሰው የራሱን ጎሣም ሆነ የዘር ግንድ የተሻለና ተመራጭ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብና መኮፈስ የለበትም፡፡ ኢስላም በሰው ልጆች መካከል አያበላልጥም፤ በቀለም በቋንቋና በዘርም ህዝቦችን አይመዝንም፣  የነቢያችንም አስተምህሮት የሚያመለክተዉ ይህንኑ ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ“ እናንተ የሰዉ ልጆች ሆይ! አምላካችሁ አንድ ነው፣ አባታችሁም አንድ ነው፣ አረቦች ዐረብ ባልሆኑት ላይ ብልጫ የላቸዉም፣ ቀይም በጥቁር ላይ ብልጫ የለውም፣ ጥቁርም በቀይ ላይ ብልጫ የለዉም፣ በአላህን ፍራቻ ቢሆን እንጂ፡፡ በላጫችሁ ይበልጥ አላህን ፈሪያችሁ ነው።’

ዛሬ ላይ ከእስልምና አስተሳሰብ በመውጣት በኢስላም ዉስጥ ቦታ የተነፈጉትን ዘረኝነትንና የመሣሠሉትን አስቀያሚ ባህሎችን ወደ ዲኑ ለመመለስ መሞከር አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ የሙስሊሙን አንድነትም ፈተና ዉስጥ መክተት ነው፡፡ ነቢዩም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ‹በጫማዬ ሥር አርጌያቸዋልና አታንሷቸዉ› በማለት መልእክት አስተላልፈዋል። ዘረኝነት ያለ ጥርጥር የገማ የአስተሣሠብ ዉጤት ነው፡፡ አራማጆቹም ከኢማን ክልል የወጡ የጠባብ አመለካከት ባለቤቶች ናቸው።

ኢስላም የሰዉ ልጆችን እኩልነት ያስተማረው በቃል ብቻ አይደለም፡፡ በተግባርም ጭምር እንጂ። በየቀኑ ከምናደርጋቸዉ ከእይታችን በማያመልጡ በብዙ የአምልኮ ተግባራት ውስጥም የምናስተውለዉም ይህንኑ ነው። ሙስሊሞች ለሰላት ሲቆሙ ሀብታምና ደሃው፣ ነጭና ጥቁሩ፣ ባለሥልጣንና ተራው ሰው እኩል ተጠጋግተዉ አንድ ላይ ሆነው ነው፡፡ ያለምንም መጠያየፍና መናናቅ። ወደ አንድ አቅጣጫ ዞረው ለአንድ አምላክ በአንድ ኢማም ይሰግዳሉ፡፡ በሰላት ኢማም ሆኖ ሙስሊሞችን የሚመራ ሰውም የሚመረጠው በቁርኣን እዉቀት ተሽሎ የተገኘዉ ነዉ ። ለተለዩ ሰዎች ተብሎ የተበጀ ቦታ የለም። ቀድሞ የመጣ ከመጀመሪያው፣ ወደኋላ የቀረ ደግሞ ከኋላ ይሠለፋል። የደሃና የሀብታም፣ የዘርና የጎሣ የመደብ ክፍፍል በኢስላም የለም።

ከሁሉ በላይ ደግሞ በታላቁ ዓመታዊ የሙስሊሞች ኮንፈረንስ በሐጅም ሥርዓት ላይ የምናየዉ  ትእይንት የሰው ልጆችን እኩልነት በግልፅ የምናይበት መድረክ ነው። ከአራቱም የዓለም ማእዘናት የተውጣጡ በሚሊየን የሚቆጠሩ ህዝቦች ተመሣሣይ ልብስ ለብሰው፤ በአንድ ድምፅ ‘ለበይከ!’ እያሉ ካዕባን ይዞራሉ፣ በሰፋና መርዋ መካከል በእርምጃ ይሮጣሉ፣ ዐረፋ ኮረብታ ላይ በለቅሦ ይቆማሉ፣ በሙዝደሊፋ ሌጣው መሬት ላይ ያድራሉ።

ያ ሁሉ ህዝብ የማይተዋወቅ ቢሆንም ኢስላም ግን እንዲተዋወቁ፣ እንዲከባበሩና እንዲዋደዱ አደረጋቸው።  ከሀብታሙ ጎን ድሃዉ አለ፣ ከምሁሩ አጠገብ ያልተማረው ይገኛል፣ ከባለሥልጣኑ ጋር ተራው ሰው ይጋፋል። ሁሉም የአላህ ባርነቱን አምኖና እራሱን አስተናንሦ ጌታዉን ይማፀናል፣ አምላኩን ይጣራል ።

ይህ ሁሉ ሲታይ ኢስላም በርግጥም ትክክለኛ የፍትሃዊነትና የእኩልነት መንፈስ የሰፈነበት ሃይማኖት መሆኑን ሣንወድ በግድ አምነን እንድንቀበል፣ ልዩ አድናቆታችንንም ለመስጠት እንገደዳለን፡፡

የኢስላም የስኬት ሚስጠሩ እዚህ ላይ ነው። አባላቱን በእኩል የፍትህ ዐይን ማየቱና አድሎንና ዘረኝነትን መቃወሙ፣  ለሰው ልጆችም እኩልነትና ነፃነት አጥብቆ መታገሉ ነው።

www.alifradio.com

ከየት አመጣኸው?

‹ማል› ማለት ገንዘብ ማለት ነው በዐረብኛ፡፡ ‹ማል›  ቋንቋዊ ትርጉሙ ‹ማዘንበል› ማለት ነው፡፡ የሰዎች ልብ ወደሱ ስለሚያዘነብሉ ነው ገንዘብ ‹ማል› ሊባል የቻለው ተብሏል፡፡ በርግጥም ወደ ገንዘብ የማያዘነብል ማን አለ!፡፡

و فتنة أمتي المال   لكل أمة فتنة ‹ለሁሉም ህዝቦች መፈተኛ አለ፡፡ የህዝቦቼ መፈተኛ ገንዘብ ነው፡፡› ብለዋል ነቢያችን ሰ.ዐ.ወ. ፡፡

ለፍተው ያገኙት ገንዘብ የላብ ዉጤት ነውና ለመስጠት እጅጉን ያሳሳል፡፡ ሆኖምግን የአላህን (ሱ.ወ.) ዉዴታ በመሻት  ብዙዎች ይሠጣሉ፣ ሳይሰስቱ ይለግሳሉ፡፡

ዛሬ ላይ ገንዘብ በውጭም ሆነ በሀገር ዉስጥ ለተለያዩ ጉዳዮች ከወዲህም ከወዲያም ይሰበሰባል፡፡ ለመስጊድ ማሰሪያ፣ ለደካሞችና የቲሞች መርጃ እና ለሌሎችም በጎ ሥራዎች ተብሎ፡፡ ይህ ገንዘብ ከግለሰብ ቢሰበሰብም እንኳን ሲደማመር የህዝብ ሀብት ነው፡፡ ከዚህ ገንዘብ ማጉደልና በምን ችግር አለውና ችላ ባይነት ለራስ ማስቀረት አንድን ግለሰብ ከመስረቅ በላይ እጅግ የገዘፈ ወንጀል ነው፡፡ ተበዳዮቹ ባለቤቶች በቁጥር ብዙ ናቸውና፡፡

በገንዘብ ጉዳይ ላይ መታመኑ እጅግ ከባድ ነው፡፡ በተለይ ዛሬ ላይ ያለውን ተጨባጭ ስናይ እውነትም ገንዘብ ትልቅ ፈተና ነው ለማለት እንገደዳለን፡፡ የአላህ ፍራቻ የሌለ እንደሆነ ለገንዘብ ሲባል የማይደረግ ነገር የለም፡፡ ዛሬ ላይ በርካታ የበጎ አድራጎት ማህበራት /ኤን ጂ ኦ/ዎች የሚቋቋሙት ሌሎችን ለመርዳት ብቻ ሳይሆን ራስንም ለመርዳት ጭምር ነው፡፡ በገንዘብ፡፡ በገንዘብ ጉዳይ አደራና ኃላፊነት የተሠጠን ሰዎች አላህን (ሱ.ወ.) እንፍራ፡፡ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ

يأيها الذين ءامنوا لاتأكلوا أموالكم بينكم بالباطل  ‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ገንዘቦቻችሁን በመካከላችሁ ያለአግባብ አትብሉ፡፡› (አን-ኒሳእ ፡29) ማለቱንም እናስታውስ፡፡

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) በወቅቱ ለነበረው መንግሥት ማጠናከሪያ የሚሆን ዘካና ግብር ሰብስበው ያመጡ ዘንድ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን ይልኩ ነበር፡፡ ሰዎቹም ከተልዕኳቸው በሚመለሱበት ጊዜ ወጭና ገቢውን ይተሳሰቧቸው ነበር፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት  ሠራተኛቸው የሆነውን ኢብኑ ሉተይበህ አልአዝዲን የተሠኘውን ሰው ላኩትና የሰበሰበውን ይዞ በመምጣት ሲያስረክባቸው እንዲህ አለ ‹ ይህ ለናንተ (የሰበሰብኩት) ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስጦታ ተሠጥቶኝ ነው፡፡›

የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) የሰውየው ንግግር አላስደሰታቸውም፡፡ ሰው ሲያጠፋ ፊትለፊት መገሰጽና በአደባባይ መወረፍ ልምዳቸው አልነበረምና ሚንበር ላይ በመውጣት አላህን ካመሰገኑና ካወደሱ በኋላ እንዲህ አሉ ‹አንድን ሠራተኛ ልኬ ይህ ለናንተ ነው፤ ይህ ደግሞ ስጦታ ተሠጥቶኝ ነው ሲል ምንድነው ነገሩ! እንዲያ ከሆነ በአባቱ አሊያም በእናቱ ቤት ቁጭ ብሎ ስጦታ ይመጣለት ወይም አይመጣለት እንደሆነ ለምን አይጠብቅም? የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ፡፡ አንድም ሰው ከሚሰበስበው ገንዘብ አንዳች ነገር ለራሱ አይወስድም፤ የቂያማ ቀን በአንገቱ ተሸክሞት የመጣ ቢሆን እንጂ፡፡ ግመል ከሆነ የግመል ድምጽ እያሰማ፣  ላምም ከሆነ የላም ድምጽ እያሰማ፣ ፍየልም ከሆነ የፍየል ድምጽ እያሰማ (ተሸክሞ ይመጣል)፡፡

በሌላም ሐዲሣቸው ‹አንድን ሰው ለሥራ ቀጥረንና ሲሳይ (ደሞዝ) ቆርጠንለት ከዚያ ዉጭ የነካ እንደሆነ ስርቆት ነው፡፡› ሙስና አሊያም ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑ ነው በዘመናችን ቋንቋ፡፡

ስለሆነም ወዳጆቼ ገንዘብ ለመሰብሰብ ኃላፊነት መውሰድ ጥንቃቄ የሚፈልግ ስለመሆኑ እናስብበት… በገንዘብ ጉዳይም አላህን እንፍራ፡፡ ዛሬ ከየት አመጣኸው ብሎ የሚጠይቀንና የሚገመገመን አካል ላይኖር ይችላል፡፡ ነገ በቂያማ ቀን አላህ (ሱ.ወ.) ከምንጠየቃቸው ከባባድ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ‹ይህን ገንዘብ ከየት አመጣኸው….› የሚለው መሆኑን ግን እንዳንረሳ፡፡ የዛሬን ኦዲተር በተለያየ ዘዴ ማምለጥ ይቻል ይሆናል አላህን ግን በፍፁም፡፡

 

የንፁህ ቀልብ አስፈላጊነት

ሙስሊሙን ኡማ አሁን ካለበት ድክመት ለማውጣት፣ ህብረቱን ለማጠናከርና በመካከሉም ፍቅርን ለማንገስ ብሎም ዲኑን ሣይሸራረፍ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ብዙ ብዙ ነገር ያስፈልገናል፡፡ ከነኚህም መካከል እስቲ ጥቂቶቹን እንቁጠር፡- አንድነት ለሙስሊሙ ኡማ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ.) ከልዩነት እንድንርቅ፣ አንድነታችንን እንድናጠናክርና በ ላኢላህ አላህ ገመድ እንድንተሳሰር የሚመክረን፡፡ ‹ሁላችሁም የአላህን ገመድ ያዙ፣ አትለያዩ› (ኣሊ ዒምራን ፡104) ብሎናል፡፡

 

አንድነት ያስፈልገናል፣ ፍቅር ያስፈልገናል፣ መቻቻልና መከባበር ያስፈልገናል፣ትምህርት ያስፈልገናል፣ መረጃ ያስፈልገናል፣ ንቃት ያስፈልገናል፣ የዲን እውቀት ያስፈልገናል፣ ፅናት ያስፈልገናል፣ ጥንካሬ ያስፈልገናል፣ የጠራ አመለካከትና ግንዛቤ ያስፈልገናል… ሌላም ሌላም.፡፡  ከነኚህ ሁሉ በፊት ደግሞ ንፁህ ቀልብ ያስፈልገናል፡፡ ንፁህ ቀልብ ሲኖረን በርካታ ነገሮችን ማሳካት እንችላለን፡፡ ጥሩ ኒያ ሲኖረን በርካታ ድሎችን እንጎናፀፋለን፡፡ ጥሩ ንያ ደግሞ የንፁህ ቀልብ ዉጤት ነው፡፡

በነገራችን ላይ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሙስሊም ነው፡፡ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ወደዚህች ምድር ሲመጣ ንፁህ እና ፈጣሪውን አላህን (ሱ.ወ.) የሚያውቅ ነጭ ልብ ይዞ ነው የሚወለደው፡፡ ነገርግን ተፈጥሯዊ እምነቱን እንዲለውጥ የሚያደርጉት ወላጆቹ ነው፡፡ ክርስቲያን ከሆኑ ክርስቲያን፣ አይሁድ አሊያም የሌላ እምነት ተከታይ ከሆኑም እምነታቸውን በማስያዝ ተፈጥራዊ እምነቱን እንዲለውጥ ያደርጉታል፡፡ ይህም ለልቡ መበላሸት አንዱ ምክንያት ነው፡፡

ትክክለኛ ካልሆነ እምነት ዉጭ ደግሞ አላህ እርም ያደረገውን ወንጀል መሥራት ልብን ያበላሻል፡፡  የሰው ልጅ አላህን (ሱ.ወ.) በመካድም ሆነ ሌሎች አላህ (ሱ.ወ. የከለከላቸውን ወንጀሎች በመዳፈር ልቡ ሊጠቁር ይችላል፡፡ አንድ ሰው ወንጀል ባበዛ ቁጥር የልቡ ጥቁረቱ እየጨመረ ይሄድና እላዩ ላይ በተደፈደፈው የኃጢዓት  ቆሻሻ ብዛት የተነሣ ጥሩና መጥፎ ነገርን ማወቅ እስኪሣነው ድረስ ይደርሣል፡፡

 

የልብ ጥቁረት ማለት መበላሸቱን ነው የሚያመለክተው፡፡ ልብ የሰውነት ንጉሥ ነውና መበላሸቱ ደግሞ በልብ ላይ ብቻ የተወሠነ ሣይሆን ለሌሎች የሰውነት ክፍሎችም የሚተርፍ ነው፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ስለዚህ ጉዳይ ሲያስጠነቅቁን እንዲህ ብለዋል ‹አዋጅ ስሙ! በሰውነት ውስጥ ቁራጭ ሥጋ አለች፡፡ በመስተካከሏ ሰውነት ሁሉ ይስተካከላል፡፡ በመበላሸቷም ሰውነት ሁሉ ይበላሻል፡፡ እሷም ልብ ናት፡፡›

አላህ (ሱ.ወ.) ቀልባቸው ይስተካከል ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ መልእክተኞቹን ወደ ሰው ልጆች ልኳል፡፡ የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ጨምሮ ቀደምት ነቢያት ሁሉ የሰውን ልብ መጥፎ ከተባሉ ባህሪዎች ሁሉ ለማፅዳት ብዙ ለፍተዋል፣ ደክመዋል፡፡

በአላህ (ሱ.ወ.) ከማጋራት፣ ከጥላቻ፣ ከክህደት፣ ከዘረኝነት፣ ከንፍቅና፣ ከመሃይምነት፣ ከምቀኝነትና ከሌሎች እኩይ ባህሪያት የፀዳ ጥሩ ማህበረሰብ መገንባት የሚቻለው በንፁህ ልቦች ነው፡፡ የሚዋደድ፣ የሚፋቀር፣ የሚተሣሰብ፣ የሚተዛዘንና ለአንድነቱ የሚጨነቅ ህዝብ መፍጠር የሚቻለው በአላህ ፍራቻ የታነፀ ንፁህ ልብ ሲኖር ነው፡፡ የአላህ ፍራቻ ዋና ምንጩ ደግሞ ልብ ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል ‹አትመቀኛኙ፤ አትጨራረቱ፤ አትጠላሉ፤ ጀርባ አትሠጣጡ፤ አንዳችሁ በሌላው ገበያ ላይ አይሽጥ፤ ወንድማማቾች የአላህ ባሮች ሁኑ፡፡ ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው፤ አይበድለውም፤ አያዋርደውም፤ አይንቀውም፡፡ ወደ ደረታቸው /ልባቸው/ ሦስት ጊዜ እያመለከቱም ‹ተቅዋ/የአላህ ፍራቻ/ እዚህ ነው፡፡›

አቢ ሁረይራ (ረ.ዐ.) በዘገቡት ሐዲስም የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ‹አላህ ወደ ቅርፃችሁና ሀብታችሁ አይመለከትም፡፡ ነገርግን ወደ ቀልቦቻችሁና ወደ ሥራዎቻችሁ ነው የሚመለከተው፡፡› ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ የነገን የትንሣኤ ቀን ስኬትን ከንፁህ ቀልብ ጋር አያይዞታል፡፡ እንዲህ በማለት

يَوْمَ لَا يَنفَعُ مَالٌ وَلَا بَنُونَ ﴿٨٨﴾ إِلَّا مَنْ أَتَى اللَّهَ بِقَلْبٍ سَلِيمٍ ﴿٨٩﴾

‹ገንዘብም ልጆችም በማይጠቅሙበት ቀን፡፡ ወደ አላህ በንፁህ ልብ የመጣ ቢሆን እንጂ፡፡› (ሹዐራእ ፡ 88-89 )

ዑለማኦች እንዳሉት ‹ሰሊም› ቀልብ ማለት በአላህ ከማጋራት፣ ከጥላቻ፣ ከምቀኝነትና ከመሣሉት መጥፎና አጠራጣሪ ነገሮች የፀዳ ነው፡፡

ሶሐቦችና ቀደምት ሰለፎች ለቀልባቸው ፅዳት እጅጉን ይጨነቁ ነበር፡፡ ኢያስ ኢብኑ ሙዓዊያ ስለባህሪያቸው ሲናገር ‹ በነርሱ ዘንድ በላጩ ሰው ልቡ ንፁህ የሆነውና ከሀሜት የታቀበው ነው፡፡› ብሏል፡፡

ሱፍያን ኢብኑ ዲናር ከቀደምት ሠለፎች መካከል አንዱ ለሆነው ለአቢ ቢሽር ‹ስለቀደሙን ሰዎች ሥራዎች ምን እንደሚሠሩ ንገረን እስቲ?› በማለት ጠየቀው፡፡ እርሱም ‹ትንሽ ይሠራሉ፡፡ ነገርግን ብዙ ምንዳ ያገኛሉ፡፡› አለው፡፡ ‹ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?› በማለት ጠየቀው፡፡ አቢ ቢሽርም ‹ልባቸው ንፁህ በመሆኑ ነው፡፡› በማለት መለሠለት፡፡

የሰው ልጆች በአላህ (ሱ.ወ.) የሚያጋሩት፣ ወንጀሎችን የሚዳፈሩት፣ የአላህን ህግጋት የሚጥሱት፣ ስለራሣቸው ትተው ስለሌላው በማውራት ብዙ ጊዜያቸውን የሚጨርሱት፣በአንድ እምነት ውስጥ ሆነው የሚወዛገቡት፣ የአንድ አባት የአደም ልጆች ሆነው ሣለ ለደም መፋሰስ የሚደርሱት፣ ዘመዳሞች የሚራራቁት፣ ጎረቤታሞች የሚኮራረፉት፣ በልባቸው ላይ ባለው ችግር የተነሣ ነው፡፡ እናም ለዚህ ላለንበት ችግር ሁሉ ንፁህ ቀልብ ያስፈልገናል፡፡ አዎን ተያይዞ ለመጓዝ፣ ከሙስሊሙም ሆነ ሙስሊም ካልሆነው ማህበረሰብ ጋር ተግባብቶ ለመኖርና ወደፊት ለመራመድ፣ ለሀገር ዕድገትና ለዓለም ሰላም፣ ብሎም በዚህ ዓለምም ሆነ በመጭው ዓለም ስኬትን ለመጎናፀፍ ከሁሉም በላይ ንፁህ ልብ ያስፈልገናል፡፡

www.alifradio.com

እነዚህ ሰባት ድንቅ ባህሪያት ቀጥለን ከምናየው የአቡ ሁረይራ ሀዲስ ውስጥ ይገኛሉ። አቡ ሁረይራ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ ይለናል፡-
سبعة يظلهم الله في ظله يوم لا ظل إلا ظله: إمام عادل، وشاب نشأ في عبادة الله، ورجل قلبه معلق بالمساجد، ورجلان تحابا في الله اجتمعا عليه وتفرقا عليه، ورجل دعته امرأة ذات منصب وجمال فقال إني أخاف الله، ورجل تصدق بصدقة فأخفاها حتى لا تعلم شماله ما تنفق يمينه، ورجل ذكر الله خاليًا ففاضت عيناه

“በዚያ ከአርሹ ጥላ በስተቀር ምንም ጥላ በሌለበት ቀን (የፍርዱ ቀን)፤ አላህ ሰባት ሰዎችን በአርሽ ጥላ ስር ያኖራቸዋል። እነሱም፡- ፍትሃዊ መሪን፣ አላህን በመገዛት ወጣትነቱን ያሳለፈ፣ ልቡ ከመስጅድ ጋር የተቆራኘን ሰው፣ ለአላህ ብቻ ብለው በአላህ መንገድ ላይ የተዋደዱንና በርሱም መንገድ ላይ የተለያዩ (ሲለያይም ለአላህ ብለው)፣ አንዲት ቆንጆ ሴት ራሷን ለዝሙት አዘጋጅታለት ‘አላህን እፈራለሁ’ በማለት እምቢ ያለ፣ በድብቅ ምጽዋት የሚሠጥ ሰው፣ ብቻውን ሆኖ አላህን ሲያስታውስ አላህን ፈርቶ አይኖቹ በእንባ የሚሞላና ጉንጮቹ የሚርሱ ሰው” (አል-ቡኻሪ 620)

በእርግጥ በዚያ ቀን ጥላ ያሻናል። የማንም ሳይሆን የአላህ ጥበቃ ያስፈልገናል፤ ከዚያን ያህል ርቀት በቃጠሎዋ የምናውቃት ፀሐይ በአንድ ስንዝር ልዩነት ስትቀርበን ሁላችን በላባችን ስንጠመቅ ሞልቶም እስከ አንገታችን ሲደርስ ያኔ በእርግጥ ጥላ ያስፈልገናል። ምንስ ጥላ ይኖራል ከአላህ ሁሉን ከሚችለው ጌታ ጥላ በስተቀር። በዚያን ወቅት ከነዚህ ሰባት ሰዎች መካከል ከሆንን የአላህን ጥበቃና ጥላ እናገኛለን። ኢንሻአላህ! እስቲ ስለ ሰባቱ ሰዎች ባህሪ ጥቂት እንበል።

ፍትሃዊ መሪ፡- ይህ የትልቅ ስልጣን ባለቤትን ብቻ አይመለከትም። ማንኛውም የትንሽም ሆነ ትልቅ ስልጣን ባለቤት ኃላፊነት የሚሰማው መሪ መሆን አለበት። አላህ ሁሉንም የሰው ልጅ ፍትሃዊ ይሆኑ ዘንድ ያዛል። ፍትሃዊነት የስልጣን ባለቤትነት ሲረጋገጥ ከባድ ይሆናል። ይሄኔ ነው የፍትሃዊነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባው። በጣም ከባዱ ደግሞ ከሚጠሉህ ሰዎች ጋር የአንተን መውደቅ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር በፍትሃዊነት መኖር ነው። ምንም እንኳ ስልጣንና ኃይል በእጅህ ቢሆን እንኳን! ይህ በእርግጥ ታላቅ ትዕግስተኝነትንና ታማኝነትን ይሻል። ጉዳዩ ግለሰባዊ ሳይሆን ማህበረሰባዊ ነው። ለዚህም ይመስላል ከሰባቱ ሰዎች የመጀመሪያ በመሆን የተጠቀሰው።
አላህን በማምለክ ላይ ወጣትነቱን ያሳለፈ፡- አላህን መገዛት በሁሉም ሰብዐዊ ፍጡር ላይ ግዴታ ነው። ጉዳዩ ግን ወጣትነት ስሜታዊነት የሚንፀባረቅበት እድሜ በመሆኑ ነው። ዓለም ያረገዘችውን ሁሉ የምትወልድበት ወቅት በወጣትነት አይን የተመለከትናት ወቅት ነው። ተቃራኒ ፆታ፣ ገንዘብና ስሜት በወጣት ላይ ያበረታሉ። እነዚህን መጋፈጥ ደግሞ በእርግጥ ትልቅ ችሎታን፣ ትዕግስተኝነትንና ቆራጥነትን ይጠይቃል። ለእነዚህ ሁሉ ስሜቶች ከተሸነፉ በኋላ በእርጅና ወቅት ለኢስላማዊው መንፈስ ራስን መስጠት የሚገርም አይሆንም። የሚገርመው የሚደንቀውም በፍርዱ ቀን የአላህን ጥላ የሚያጋነውም እነዚህን ፈተናዎች በሚገባ ተቋቁሞ አላህ በመገዛት ያሳለፈ ወጣት ነው።
ልቡ ከመስጅድ የተቆራኘ ሰው፡- በዚህ ገለፃ ወቅት ነቢዩ /ሰ.ዐ.ወ/ የተጠቀሙት የአረብኛ ቃል (ሙአለቅ) የሚለውን ነው። በቀጥታ ሲተረጎምም የተንጠለጠለ ማለት ነው። ይህን ኢማም ማሊክ የተባሉ የኢስላም አዋቂ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ:- “ይህ ሰው ወደ መስጅድ ይመጣል፤ ከመስጅድ ሲወጣ ግን በፍጥነት የሚመለስበትን ጊዜ እየናፈቀ ነው።” በእርግጥ የሰዎች ልብ ከስራቸው፤ ከቤተሰቦቻቸውና ከንግዳቸው ላይ የተንጠለጠለ ነው። መስጅድ የቅድሚያ ፍላጎታቸው አይደለም። ነገር ግን አላህን በእውነት ለሚወዱ ሰዎች በምድር ካለ ቦታ ሁሉ መስጅድ ለነርሱ ተወዳጅ ስፍራ ነው። የቅድሚያ ፍላጎታቸውም የአላህን ቤት መጠበቅና በውስጡም ዘውታሪ መሆን ነው። ታዲያ ለነዚህስ የአላህን ጥላ አይገባቸውምን? አላህም በእርግጥ በነገሮች ሁሉ ውስጥ አዋቂ ነው።
ለአላህ ብለው የተዋደዱ ሁለት ሰዎች፡- ፍቅር የማህበረሰባችን ቋሚ ነው። ያለውዴታ የተሟላ ማህበረሰብን መገንባት የማይታሰብ ነው። ኢስላም ከሁሉም ሰዎች ጋር በፍቅርና በርህራሄ እንድንኗኗር ያዛል። ነገር ግን ውዴታው የአላህን ውዴታ በመሻት ለአላህ ብቻ ተብሎ ሲሆን ደግሞ የልቅናን ማማ ይቆናጠጣል። ውዴታውም የተባረከ ይሆናል። ጉዳያቸው ሁሉ አላህን በማስደሰት ላይ ስለሚገነባም ለራሳቸውም ሆነ በዙሪያቸው ላሉት ሁሉ መልካምን ይለግሳል። ይህን አይነቱ ውዴታ እውነትን፣ ታማኝነትን፣ የተላበሰ ውዴታም በመሆኑ የአላህን በረከት ይቸራል፣ ዘለዓለምም የእዝነት መሠረት ይሆናል። እነኚህስ አይገቡምን? የአላህ ጥበብ በእርግጥ ሰፊ ናት!!
ቁርጠኝነት የተላበሰ የመልካም ባህሪ ባለቤት፡- ነቢዩ /ሰ.ዐ.ወ/ ስለዚህ ሰው ድንቅ ባህሪ ሲያወሱ የተጠቀሙት የአረብኛ ቃል “መንሰብ” የሚለውን ሲሆን ይህ ማለት ሁሉንም ያሟላች ሴት (ቁንጅና፣ ሀብት፣ ጥሩ ዘርና የተከበረ ቤተሰብ) ማለት ነው። ይህን ሁሉ ያላት ሴት ማንም ሰው በሌለበት ይህንን ከባድ የስሜት ጥያቄ ስታቀርብ እምቢ፣ አሻፈረኝ ማለት ድንቅ የአላህን ፍራቻ ያመላክታል። ታላቁ የኢስላም አዋቂ ኢብን ሀጀር አል አስቀላኒ ሐዲሱ በተከበረ፣ መልከ መልካምና ሀብታም ወንድ ጥያቄ ያልተሸነፈችን ሴትንም ያመላክታል ይላሉ። በእርግጥም ይህንን ጥያቄ አሻፈረኝ ማለት ጠንካራ ስብዕናን ይሻል። በአላህ ፍራቻ ልባቸው የተሞላ ግን ይህን አማላይ ጥያቄ አሻፈረኝ ለማለት አያንገራግሩም። ታዲያ የአላህ ጥላ አይገባቸውምን? የአላህ ራህመት ምንኛ ሰፋች!
ለዝና ብሎ የማይለግስ ቸር፡- የዚህ ሰው ባለቤት የራሱ ግራ እጅ በማይመለከትበት ሁኔታ ቀኝ እጁ ይሰጣል ማለት ለመስጠቱ ምላሽን ከሰዎችም ሆነ ከራሱ አይሻም። ይልቁንም የሥራውን ምስጋና ከአላህ ብቻ ይጠብቃል። የሰዎች ምስጋና ፍላጎት ፈፅሞ አይቀይረውም። ፍላጎቱ አላህን ማስደሰት ብቻ ነው። ይህ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀው አሰጣጥ ነው ሽልማቱም አርሽ ጥላ ስር መቀመጥ ነው።
አላህን ብቻውን ባስታወሰው ጊዜ ጉንጮቹ በእንባ የሚርሱ ሰው፡- አላህን ብቻ በማሰብ፣ ድንቅ ባህሪያትን እና ስሞቹን በማስታወስ፣ እርሱንም በማመስገንና በማወደስ የምታልፍ ሰዓት ከሰዓቶች ሁሉ እጅግ የተዋበችዋ ሰዓት ነች። አላህን ማስታወስ በማንኛውም ወቅት የሚተገበር የአምልኮ አይነት ሲሆን ስሙም “ዚክር” ይባላል። ማንም በማይመለከትህ ሰዓት፣ ልብህ ከአላህ ጋር ሲገናኝ፣ ውለታዎች ስታስታውስና አይኖችህ በእንባ ጎርፍ ሲሞሉ ጉንጮችህ በዚህ የተቅዋ (አላህን ፍራቻና ጠንቃቃነት) ዶፍ ሲናጡ በእርግጥም ለአላህ ያለህን ውዴታና ተቅዋ ያመላክታል። የአላህን ፊት መሻትህን ያስገነዝባል። አላህን በእውነት የወደዱ ደግሞ በእርግጥ ስኬትን ይጎናፀፋሉ። በዚያች የጭንቅ ቀንም የአርሽ ጥላ ስር ይጠለላሉ።

እነዚህ ሰባት ድንቅ ባህሪያት እውነተኛ እምነትን፣ ቁርጠኛ አቋምን መለኪያ ሚዛን ናቸው። ስሜት፣ መንፈስን፣ አስተሳሰብንና ተግባርን ባማከለ ሁኔታ ለአላህ ያለንን ውዴታ ያሳያሉ። እነዚህ የምርጥ አማኞች ባህሪያት ናቸው። አላህ እነዚህን ባህሪያት በእውነት ከሚጎናፀፉት ሰዎች ያድርገን። ሁላችንንም በጭንቁ ቀን በእርሱ አርሽ ጥላ ስር ያኑረን። አሚን!!!
source=http://ethiomuslims.net

ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያደርጉት ከሚገባቸው ነገር ውስጥ አንዱና ዋነኛው ልጆች በራሳቸው ላይ እምነት እንዲያሳድሩና ስለራሳቸው አዎንታዊ እይታ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።

በራስ ላይ እምነት መጣል (በራስ መተማመን) አዎንታዊ የሆነ ማህበራዊና ውስጣዊ መስተጋብር በመፍጠር ረገድ ቁልፍ ቦታ አለው። ከፍተኛ የራስ መተማመን ያላቸው ልጆች በራሳቸው ጥሩ ውሳኔ ይወስናሉ፣ በሥራቸውም ኩሩዎች ናቸው። ኃላፊነትን ለመቀበል ፍቃደኞችና በከባድ (አስፈሪ) ሁኔታዎችም ውስጥ ለማለፍ ዝግጁዎች ናቸው። በማህበራዊ ህይወታቸው ውጤታማ፤ በትምህርት ቤትም ውስጥ ተፎካካሪዎች፤ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እንደ ትምህርት “መፎረፍና” ዕፅ መጠቀምን የሚያስወግዱ ናቸው።

ወላጆችና አካባቢ በልጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመንን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ልጆች እንደሚደመጡ ማሰብ ሲጀምሩና ሠዎች ከእነሡ ቁምነገር እንደሚጠብቁ ሲያውቁ ከልባቸውም እንደሚንከባከቧቸው ሲያስቡ በራሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ ይሆናል። ከዚህ በታች የልጆቻችንን በራስ መተማመን የሚያዳብሩ ነጥቦች ተጠቅሠዋል።

1. ተሰጥኦዎቻቸውን ተንከባክቦ ማሣደግ

ማንኛውም ልጅ አፈጣጠሩ ለአላህ እጅ የሠጠ (ፊጥራ) ሆኖና አንድ ልዩ ተሰጥዖ ይዞ ነው። ከዚያ በኋላ ግን ከእድገት ጋር ተያይዞ አዳዲስ ባህሪያት (ማንነቶች) ይመጣሉ። እነዚህ ተሰጥዖዎች ልዩ ለሆነ ዓላማ ነው የተፈጠሩት። እናም ልንከባከባቸውና በሙሉ አቅማቸው እንዲያድጉ ልናደርግ ይገባል። በዚህ ረገድ ታዲያ ወላጆች ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። በመጀመሪያ እነዚህን ተሰጥዖዎች ለይቶ በማውጣቱ ረገድ ከዚያም እነዚህ ተሰጥዖዎች በማሣደግ ረገድ መንገዶችን በሚፈላለጉ በኩል። በርግጥ ይህ ሥራ ልጆች እያደጉ በመጡ ቁጥር ቀላል ይሆናል። ነገር ግን፤ አንዳንድ ተሰጥዖዎች በጣም በትንሽ ዕድሜ ውስጥም የሚታዩ (የሚኖሩ) ናቸው። ትምህርት፣ ዝንባሌዎች፣ ስብስቦች፣ ስፖርቶችና ሌሎችም ፍላጎቶች እነዚህን ልዩ ተሠጥዖዎች የምንከባከብባቸው አጋጣሚዎች ናቸው። ይህ ነጥብ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ብዙ ጊዜ የሚረሡ የሆኑትን ሴት ህፃናትም ያጠቃልላል። የልጆች ተፈጥሮአዊ ችሎታዎችን እድገት መቅጨት በልጆች የራስ መተማመን ላይ ግልፅ የሆነ ተጽዕኖ ያሳድራል። አንደ ልጅ ከችሎታውና ከፍላጎቱ ጋር የማይሄድ ዘርፍ ውስጥ እንዲገባ ከተገደደ በራሡ ላይ የሚኖረው እምነት አነስተኛ ይሆናል። ወላጆቹም የሚጠብቁበትን ነገር አያገኙም።

2. ከልጆች ጋር መወያየት

በኢትዮጵያውያን ላይ የተሠራ ጥናት ባይኖርም፤ አስገራሚው የቁጥር መረጃ እንደሚሳየን አንድ አሜሪካዊ ልጅ በሳምንት በአማካይ 1680 ደቂቃዎችን በቴሌቪዢን ላይ በማፍጠጥ ሊያሳልፍ 38.5 ደቂቃውን ብቻ ነው ከቤተሠቦቹ ጋር ትርጉም ያለው ውይይት በማድረግ የሚያሳልፈው። በእንደዚህ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ ታዲያ የልጆች ማህበራዊ ጉድለት ማነስና የቤተሠብ በብዙ ችግሮች ውስጥ መዘፈቅ ምንም አያስገርም። ለልጆች በራስ መተማመን ማደግ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ብዙ ምክንያቶች ሲባል ወላጆች በየቀኑ ከልጆቻቸው ጋር መነጋገራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ጥሩ መስተጋብር ለመፈጠር ዋነኛ መንገድ መደማመጥ ነው (በደንብ መደማመጥ)። ማለትም የልጃችንን ሃሳብና ስሜት ለመረዳት እንሞከር። ሀሳቡ ስሜቱና ፍላጎቱ ባጠቃላይ ትኩረት ሊሠጣቸው ይገባል። ወላጅ ልጁ የሚሠራው ሥራ ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን ሊያሣየውና ስለአስፈላጊነቱ ሊያወራው ይገባል። በርግጥ የኛን አመለካከትና እምነት ማብራራት ይኖርብናል። ነገር ግን፤ ይህ መሆን ያለበት በተለያየ መንፈስና ምክንያታዊነት ሊሆን ይገባዋል።

ችግሮች የልጆችን ማንነትና ባህሪ በማያቃውስ መልኩ ሊመሩ ይገባል። ልጆች ችግር እያለባቸው በችግራቸው ግን አለመቀወሳቸውን ሲረዱ ለችግራቸው ከምንጊዜውም በተሻለ መልኩ መፍትሄ ይፈልጉለታል።

3. ኃላፊነትንና ራስን መቻል ማስተማር (መገንባት)

በመጨረሻም ልጆቻችን ፈሪሀ-አላህ ያላቸውና በራሳቸው ውሳኔ መወሠን እንዲችሉ ማድረግ እንፈልጋለን። የዚህ ጤናማ የሆነ በራስ መተማመንና ውሳኔ የመስጠት አንዱ ክፍል ደግሞ እነዚህን ክህሎቶች ለመማርና ለማሳደግ ዕድል ማግኘት ነው። ወላጆችም ልጆቻቸው የውሳኔ ሰጪነትና የችግር አፈታት ክህሎትን እንዲማሩና በዕለት ተዕለት ህይወታቸው ውስጥ እንዲተገብሩት ሊያበረታቷቸው ይገባል። እነዚህ ክህሎቶች ለልጆቻችን ኃላፊነትን በመስጠትና ቀስ በቀስ የራሳቸውን ህይወት እንዲመሩ ነፃነት በመስጠት እውን ሊሆን ይችላል።

በተለይም ልጆች እያደጉ ሲመጡ የምንሠጣቸው ኃላፊነት ዕድሜያቸውን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባና ምክንያታዊ ሊሆን ይገባዋል። ወላጆችም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሁሉ ሊረዷቸው ግድ ነው። ይህ ዕድል ያላቸው ልጆች ራሳቸውን ጠቃሚ፣ ገንቢ ዋጋ ያላቸውና ተፎካካሪ እንደሆኑ ያስባሉ። ታዲያ ይህ በራሡ በወላጆችና በልጆች መሀል ያለውን መተሣሠብ (እምነት) ይጨምራል።

4. ከምንም ነገር በላይ ልጅህን ውደድ

ይህ ማለት ልጅህን ምን ያህል እንደምትሳሳለት/ላት ማሣየትና እንደምትወደው/ዳት ሁሌም ቢሆን መንገር ነው። ከልጅህ ጋር ጊዜ ሠጥተህ ማሣለፍ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መጫወት፣ ማውራት ምርጥ የሚባሉ ክስተቶችን አብሮ ማሣለፍ የእግር መንገዶችን አብሮ መሄድ፣ መፅሀፍ እንዲሁም ቁርኣን መቅራትና ሌሎች ብዙ ብዙ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ወላጆች ከልጆች ጋር በሚያወሩበት ወቅት የልጆችን በራስ መተማመን የሚገነቡ ቃላት መጠቀም አለባቸው። ለምሳሌ “አመሠግናለሁ”፤ “በጣም ጥሩ ሃሳብ”፣ “የምትገርም ልጅ ነህ”፣ “በሥራህ ኮራሁ”፣ “ማሻአላህ” እና ሌሎችም። ልክ እንደ ዱአ እና ሌሎች ልዩ አድናቆቶች ሁሌም በምስጋና ጀርባቸውን መታ እያደረጉ እያቀፉ በመሣም በሌሎችም የተለያዩ መንገዶች ለልጆቻችን ያለንን ቀረቤታና ፍቅር ማሣየት ያስፈልጋል። ከምንም በላይ ደግሞ ውዱ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ለልጆች በጣም ቅርብ አዛኝና ተንከባካቢ እንደነበሩ ማስታወስ ተገቢ ነው።

ባጠቃላይ ከላይ የጠቀስናቸው የልጆችን በራስ መተማመንና በራስ ላይ እምነት መጣል ለማሣደግ ከምንጠቀማቸው መንገዶች ውስጥ የተወሠኑት ብቻ ናቸው። ልጆች አንዴ ስለራሳቸው አዎንታዊ የሆነ አመለካከት መገንባት ከቻሉ በህይወታቸው ውስጥ ሊገጥማቸው የሚችሉ ሌሎች ችግሮችን መጋፈጥ ይችላሉ። በዚህም ስኬታማ፣ ተፎካካሪ እና በራሳቸው እምነት ያላቸው ይሆናሉ። ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመን ማሣደግ ጥቅሙ ለልጆች ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ለቤተሰቡ ነው። ይህ ነገር የልጆችና የቤተሠብን መስተጋብር በማጠናከር የልጆችና የወላጆች ግንኙነት እንዲያምር በማድረግ አላህ የሚፈልገው አይነት ቤተሠብ እንዲፈጠር ያደርጋል።

source= ethiomuslimsnet

ንጽህና

ኢስላም በበርካታ ድንጋጌዎች ልጆቹን በንጽህና ያዛል፡፡ ሁሌም ንጹህና ማራኪ እንዲሆኑ ይሻል፡፡ አካላቸውን ታጥበውና አጽድተው፣ ልብሳቸውን አጥበው ንጽህናቸውን ጠብቀው፣ ሽቶ አርከፍክፈው ማራኪ ሽታ ከነርሱ እንዲመነጭ ያስተምራቸዋል፡፡

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በባህሪያቸው እንዲህ ነበሩ፤ ሁሌም ንጹህና ማራኪ ሽታ ነበራቸው፡፡ ሙስሊም እንደዘገቡት ማሊክ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ብለዋል፡-

“ከአላህ መልእክተኛ ይበልጥ የሚያውድ ሽታ ያለው ሚስክ ወይም ሽቶ አሽትቼ አላውቅም፡፡” (አቡ ዳውድ)

የነቢዩን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የአካልና የልብስ ንጽህና የሚያወሱ፣ ሽታቸውና ላበታቸው እጅግ ይማርኩ እንደነበር የሚገልጹ ዘገባዎች በርካታ ናቸው፡፡

አንድን ሰው በመዳፋቸው ከጨበጡት ያ ሰው ከእጁ ላይ የሚቀረውን ሽታ ቀኑን ሙሉ እያጣጣመ ይውላል፡፡ እጃቸውን ከአንድ ልጅ ራስ ላይ ሲያስቀምጡ ያ ልጅ ከሌሎች ልጆች መሐል በማራኪ ሽታው ተለይቶ ይታወቃል፡፡ ቡኻሪ ጃቢርን በመጥቀስ እንደዘገቡት ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በአንድ መንገድ ሲያልፉ ጠረናቸውን መከተል ይቻል ነበር፡፡

አንድ ቀን ከአነስ ቤት ተኙ፡፡ ላበት ወጣቸው፡፡ የአነስ እናት እቃ አመጣችና ላበታቸውን እየጠረገች ከእቃ ውስጥ ታደርግ ጀመር፡፡ ለምን እንዲህ እንደምታደርግ መልእክተኛው ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጠየቋት፡፡ “ከሽቶ ጋር ልቀላቅለው ነው፡፡ የርስዎ ላበት ከየትኛውም ሽቶ የበለጠ ይጣፍጣል፡፡” አለች፡፡ (ሙስሊም)

‎ኢትዮሙስሊምስ‬